ሩሲያ በበኩሏ ገንዘባቸው ለዩክሬን የተሰጠባቸው የአውሮፓ ገበሬዎች መንግስታቸውን መጠየቅ ጀምረዋል ብላለች
የአውሮፓ ገበሬዎችን ወደ አደባባይ ለተቃውሞ ያወጣቸው ምክንያት ምንድን ነው?
የአውሮፓ ገበሬዎች ለተቃውሞ ወደ አደባባይ መውጣት ከጀመሩ አንድ ወር ያለፋቸው ሲሆን ጀርመን ፣ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድ፣ ሮማኒያ እና ፖላንድ ደግሞ አመጹ እየተካሄደባቸው ካሉ ሀገራት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ከሰሞኑ ተቃውሞ ከበረታባቸው ሀገራት መካከል ፈረንሳይ ስትሆን ለገበሬዎቿ አመጽ ምክንያት የሆነው የነዳጅ ዋጋ መናር፣ ለግብርና ስራዎች በመንግስት ይደረጉ የነበሩ ድጎማዎች መነሳታቸው እና የግብር መጨመር ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው።
በመንግስት አዲስ ፖሊሲዎች የተበሳጩት ገበሬዎችም ትራክተሮቻቸውን እና ሌሎች የግብርና መሳሪያዎቻቸውን በመያዝ ወደ አደባባዮች ወጥተዋል።
የፈረንሳይ መንግሥት ወጪውን ለመቀነስ በሚል ያወጣቸው አዳዲስ ፖሊሲዎች ገበሬዎችን እስከ 47 ሚሊዮን ዩሮ ተጨማሪ ወጪ እንዲያወጡ የሚያደርጉ ናቸው ሲል ዩሮ ኒውስ ዘግቧል።
ሌላኛው የገበሬዎች አመጽ እየተካሄደባት ያለችው ሀገር ጀርመን እና ኔዘርላንድ ሲሆኑ ገበሬዎቹ የሀገራቸውን ዋና ዋና መንገድ እና የህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት መኖሪያ ቤቶችን በግብርና ተረፈ ምርቶች ዘግተዋል።
መንግስታቸው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚል የወሰዳቸው የፖሊሲ ማሻሻያዎች ገበሬዎቹን ወደ አደባባይ ካወጡ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ገበሬዎቹ ወደ ግብርና ኢንቨስትመንት ስራ የገባነው ከዚህ በፊት የነበሩ መንግስታት ባስተላለፉት ጥሪ ሙሰረት ነው አሁን ደግሞ በመንግስት ፖሊሲዎች ምክንያት ጫና ውስጥ እንድንገባ ተደርገናል ሲሉ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ተናግረዋል።
የነዚህ ገበሬዎች አመጽ በቀጣይ በሚደረጉ ምርጫዎች ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ተገልጿል።
በተለይም በምስራቅ አውሮፓ ባሉ ሀገራት በተለይም በፖላንድ፣ ሮማንያ፣ ስሎቫኪያ፣ ሀንጋሪ እና ቡልጋሪያ ጉዳዩ የፖለቲካ አጀንዳዎች እየሆኑ ነው ተብሏል።