የእስራኤልና የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከአውሮፓ ህብረት አቻዎቻቸው ጋር ይመክራሉ
ህብረቱ የጋዛውን ውጥረት የሚያረግብና ዘላቂ ሰላም የሚያሰፍን የሰላም ጉባኤ ለማዘጋጀት ጥረት እያደረገ ነው
በብራሰልሱ ምክክር የግብጽ፣ ሳኡዲ አረቢያና ዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም ይሳተፋሉ
የእስራኤልና የፍልስጤም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው እለት ከአውሮፓ ህብረት አቻዎቻቸው ጋር ይመክራሉ።
እስራኤል ካትዝ እና ሪያድ አል ማሊኪ በተናጠል ከህብረቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የሚያደርጉት ምክክር ዘላቂ ሰላም ማስፈን የሚያስችል የሰላም ጉባኤ ለማስጀመር መደላድል ይፈጥራል ተብሏል።
በብራሰልሱ ምክክር የግብጽ፣ ሳኡዲ አረቢያ እና ዮርዳኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የአረብ ሊግ ዋና ጸሃፊ እንደሚሳተፉ መገለጹንም ሬውተርስ ዘግቧል።
የአውሮፓ ህብረት ሁሉን አካታች የእስራኤልና ፍልስጤም የሰላም ጉባኤ ለማስጀመር ያዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ ለ27ቱ አባል ሀገራት ልኳል።
ዋናው የሰላም ጉባኤ ከመደረጉ በፊትም የቅድመ ጉባኤ ምክክሮችን ግብጽ፣ ዮርዳኖስ፣ ሳኡዲ አረቢያና የአረብ ሊግ እንዲያመቻቹ፤ አሜሪካ እና ተመድም እንዲሳተፉ ይጠይቃል የህብረቱ ፍኖተ ካርታ።
የአውሮፓ ህብረት እጠራዋለሁ ባለው የሰላም ጉባኤ ግን እስራኤልም ሆነች ፍልስጤም እንደማይሳተፉ ማሳወቃቸው ይታወሳል።
የህብረቱ የሰላም እቅድ ራሷን የቻለች ፍልስጤም እውን እንድትሆን የሚጠይቅ መሆኑን ሬውተርስን ጨምሮ ሰነዱን የተመለከቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
እስራኤል ግን ይህን የህብረቱን የሰላም እቅድ እንደማትቀበለው ገልጻለች።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ባለፈው ቅዳሜ በስልክ ሲወያዩ እስራኤል ከጋዛ እንደማትወጣና የጸጥታ ሃይሉን እንደምትቆጣጠር መግለጻቸው ይታወሳል።
ይህም ቴል አቪቭ ወደ ጋዛ ስትገባ ካስቀመጡት ሃማስን የመደምሰስ ተልዕኮ ባሻገር ተጨማሪ ግብ መያዙን አመላክቷል።
ኔታንያሁ የፍልስጤምን ሀገር መሆን በድጋሚ እንደማይቀበሉ መናገራቸው የአሜሪካ ፖለቲከኞችን ለሁለት ከፍሏል ነው የተባለው፤ የአውሮፓ ህብረትና ብሪታንያም መሰል ንግግሮች ጦርነቱን ያባብሰዋል በሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ “ከጋዛ አንወጣም” ንግግር አዲስ ባይሆንም ሶስት ወራት ያስቆጠረውንና ከ25 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን የተገደሉበትን ጦርነት ያራዝመዋል የሚለውን ስጋር አንሮታል።