ከ50 በላይ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች የትራምፕ መመረጥ በአህጉሩ ስለሚፈጥረው ተጽዕኖ እየመከሩ ነው
የኔቶ ዋና ጸሃፊ የሩስያ እና ሰሜን ኮርያ ጥምረት ለአሜሪካም የደህንንት ስጋት ነው ብለዋል
መሪዎቹ በዛሬው እለት በሀንጋሪ ቡዳፔስት ለአንድ ቀን የሚቆይ ጉባኤ በማኬድ ላይ ናቸው
50 የሚጠጉ የአውሮፓ መሪዎች የዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኖ መመረጥ በአህጉሩ እና በባለብዙ ወገን ድርጅቶች ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ እየገመገሙ ነው፡፡
በስብሰባው ላይ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዘለንስኪ እና የኔቶ ዋና ፀሀፊ ማርክ ሩትን ጨምሮ የአውሮፓ ሀገራት እና ድርጅቶች መሪዎች ተገኝተዋል፡፡
መሪዎቹ በሩስያ ጉዳይ በጆባይደን የስልጣን ዘመን እንዳለው ጠንካራ የጋራ አቋም እንዲንጸባርቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩት በስብሰባው ባደረጉት ንግግር “ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ የተለያዩ የሚሳኤል እና የሳተላይት ቴክኖሎጂዎችን በመስጠት በምላሹ ከፒዮንግያንግ ወታደራዊ ድጋፍ እያገኘች ነው ይህ ለአውሮፓ የኔቶ ክፍል ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካ ደህንነትም ከፍተኛ ስጋት ነው” ብለዋል፡፡
ትራምፕ በመጀመርያው የፕሬዝዳንትነት ጊዜያቸው የኔቶ አባል ሀገራት ለድርጅቱ የመከላከያ ወጪ የሚጠበቅባቸውን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 2 በመቶ እና ከዛ በላይ እንዲያወጡ እንዲሁም ከአሜሪካ ወታደራዊ እገዛ ጥገኝነት እንዲላቀቁ በጥብቅ ይገፋፉ ነበር፡፡
ይህንኑ ሀሳብ የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርልስ ሚሼል በዛሬው ስብሰባ ላይ ያነሱ ሲሆን አህጉሩ በአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ እና የኔቶ መዋጮ ላይ ጥገኛ ከመሆን መላቀቅ አለበት ብለዋል፡፡
የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት “አውሮፓ ካማላ ወይም ትራምፕ ስለተመረጡ ሳይሆን የራሱን እጣፈንታ የሚወስንበትን አቅም ሊገነባ ይገባል” ነው ያሉት፡፡
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከአውሮፓ ጋር ከሚኖረው የንግድ ጦርነት አንስቶ ከኔቶ ለመውጣት እና ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት መሰረታዊ የሆነ የድጋፍ ለውጥ እንደሚያደርጉ ዝተዋል፡፡
ይህም በመላው አውሮፓ በሚገኙ ሀጋራት ላይ ከፍ ያለተጽዕኖ ሊያስከትል እንደሚችል ኤፒ ዘግቧል፡፡
በ 2018 የትራምፕ አስተዳደር የውጭ ምርቶች በአሜሪካ አጋሮች ቢመረቱም ለአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አስጊ ናቸው በሚል በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በሚመረቱ የብረት እና አሉሚኒየም ምርቶች ላይ የታሪፍ ጨማሪ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል የአውሮፓ ሀገራት ትራምፕ የዩክሬን ጦርነት ለማስቆም በሚያደርጉት ጥረት ለሩስያ ሊያደሉ እንደሚችሉ ስጋት አላቸው፡፡
50ዎቹ መሪዎች የተሰባሰቡበትን ጉባኤ ያዘጋጀችው ሀገር ሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ከትራምፕ ጋር በስልክ እንደተነጋገሩ እና የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ትልቅ እቅድ እንዳላቸው ከስብሰባው በፊት ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ምርጫ ውጤት በዩክሬን እና በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ፣ በስደት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከቱ ጉዳዮች ለሚቀጥሉት አመታት በአውሮፓ አጠቃላይ ግንኙነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡