የአውሮፓ መሪዎች ለአረብ ሀገራት የጋዛ መልሶ ግንባታ እቅድ ድጋፍ ሰጡ
53 ቢሊየን ዶላር የሚያስፈልገው እቅዱ ጋዛን በ5 ዓመታት ውስጥ መልሶ መገንባት የሚያስችል ነው

ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያንና ጀርመን እቅዱ በጦርነት የተጎዳችውን ጋዛን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ነው ብለዋል
የአውሮፓ መሪዎች የአረብ ሀገራት ጋዛን መልሶ ለመገንባት ያስችላል በሚል ላጸደቁት እቅድ ድጋፋቸውን ሰጡ።
ግብፅ ያቀረበችውና 53 ቢሊየን ዶላር የሚያስፈልገው የጋዛ መልሶ ግንባታ እቅድ በአረብ ሀገራት መሪዎች ባሳለፍነው ሳምንት መጽደቁ ይታወሳል።
የጋዛ መልሶ ግንባታ እቅድ በአረብ ሀገራት ከጸደቀ በኋላ የተለያዩ የዓለም ሀገራት በእቅዱ ላይ አስተያየት እየሰጡ ይገኛሉ።
የፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ኢጣሊያ እና ጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰቴር መስሪያ ቤቶች በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ በ53 ቢሊየን ዶለር ጋዛን መልሶ ለመገንባት ለቀረበው እቅድ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡ አስታውቀዋል።
እቅዱ ጋዛን መልሶ ለመገንባት ተጨባጭ መንገድ ነው ያሉት ሀገራቱ፤ እቅዱ ተግራዊ ከተደረገ በጋዛ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ፍሊስጤማውያንን ህይወት ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማሻሻል የሚረዳ ነው ብለዋል።
ሃማስ "ከእንግዲህ ጋዛን ማስተዳደር የለበትም ወይም ለእስራኤል ስጋት መሆን የለበትም" ያሉት አራቱ ሀገራት በጋዛ መልሶ ግንባታ የፍልስጤም አስተዳደር የሚኖረውን ሚና እና የተሃድሶ አጀንዳውን አፈፃፀም እንደሚደግፉም አስታውቀዋል።
የአረብ ሀገራ መሪዎች ባሳለፍነው ሳምንት በካይሮ ባደረጉት ስብሰባ የጋዛን መልሶ ግባታ እቅድ ካጸደቁ በኋላ የተለያዩ የድጋፍ እና የተቃውሞ ድምጾች እየተሰሙ ይገኛሉ።
57 አባል ሀገራትን በውስጡ የያዘው ዓለም አቀፉ የእስልምና ትብብር ድርጅት (ኦአይሲ) በትናንትናው እለት በሳዑዲ አረቢያ ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ እቅዱን በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ አጽደቆታል።
ጋዛን የሚያስተዳድረው ሃማስ እቅዱ በአረብ ሀገራት ተቀባይነት አግኝቶ መጽደቁን ተከትሎ ጋዛን በፊሊስጤም አስተዳደር ስር መልሶ ለመገንባት በአረብ ሀገራት የተደረሰውን ውሳኔ በደስታ እንደሚቀበለው አስታውቋል።
"ጋዛን መልሶ የመገንባት እቅድ በደስታ እንቀበላለን” ያለው ሃማስ፤ ለስኬታማነቱ የሚያስፈልጉ ሁሉም ጥረቶች እንዲደረጉም ጥሪ አቅርቧል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በበኩሉ ግብጽ ጋዛን መልሶ ለመገንባት ያስችላል በሚል ያቀረበችውን እቅድ ውድቅ አድርጓል።
እቅዱ "ጋዛ በአሁኑ ጊዜ ለመኖሪያነት አመቺ አለመሆኗን እንዲሁም ነዋሪዎቿ በፍርስራሾች እና ባልተፈነዱ ፈንጂዎች ውስጥ መኖር አይችሉም የሚለውን እውነታ አለተመለከተም" ብሏል።
እስራኤልም ግብጽ ጋዛን መልሶ ለመገንባት ያስችላል በሚል ያቀረበችውን እቅድ “መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ” ነው በሚል ውድቅ አድርጋለች።
የግብጽ የጋዛ መልሶ ግንባታ እቅድ በውስጡ ምን ይዟል?
ከጋዛ መልሶ ግንባታ ጋር በተያያዘ ግብፅ ትራምፕ "የጋዛ ሪቪዬራ" እቅድ አማራጭ የሆነ እቅድ ይፋ ያደረገች ሲሆን፤ እቅዱ 53 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ እና አምስት አመታትን እንደሚወስድ ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ግብጽ ያዘጋጀችው እቅድ ፍልስጤማውያን "በመሬታቸው እንዲቆዩ" የሚያስችል ነው ብለዋል።
በእቅዱ መሰረት የመጀመሪያው ስድስት ወራት የማገገሚያ ምዕራፍ ሲሆን፤ በዚህም ፍርስራሾችን በማንሳት እና በ3 ቢሊዮን ዶላር ጊዜያዊ መኖሪያ ቤቶችን መገንባት ላይ ያተኮረ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚሁ ምዕራፍ 200 ሺህ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና 60 ሺህ ህንጻወችን የማደስ ስራ እንደሚከናወንም በእቅዱ ተመላክቷል።
በእቅዱ መሰረት በፈረንጆቹ በ2030 እቅዱ ለ3 ሚሊዮን ሰዎች ሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ቤቶች ግንባታ እንዲሁም የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የኢንዱስትሪ ዞኖች፣ ሆቴሎች እና መናፈሻ ፓርኮች ግንባታ እንደሚጠናቀቅም ተመላክቷል።
የአረብ ሀገራት አስቸኳይ ጉባዔ ላይ የቀረበው የጋዛ እቅድ ጋዛን የመካከለኛው ምስራቅ ሪቬራ አደርጋለሁ ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ያቀረቡትን የሚፎካከር ነው።
ፕሬዝደንት ትራምፕ አሜሪካ ጋዛን በቁጥጥሯ ስር እንደምታደርግ፣ 2.2 ሚሊዮን ገደማ ነዋሪዎቿን ወደ ሌላ ሀገር እንደምታዛውርና "የመካከለኛው ምስራቅ ውብ ቦታ" እንደሚያደርጉ መናገራቸው የአረቡን አለም አበሳጭቷል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ የአረብ ሀገራት በተለይም ግብጽና ጆርዳን 16 ወራት በዘለቀው የእስራኤል-ሀማስ ጦርነት የወደመችው ጋዛ እስከምትጸዳና መልሳ እስከምትገነባ በጋዛ ያሉ ፍልስጤማውያንን እንዲያስጠልሏቸው ጫና ሲያደርጉ ቆይተወዋል።
ነገርግን የአረብ ሀገራት ትራምፕ ያቀረቡትን ሀሳብ በጽኑ ተቃውመውታል።
የአረብ ሀገራት ፍልስጤማውያን ከቦታቸው ሳይፈናቀሉ የመልሶ ግንባታው አካል መሆን ይጠባቸዋል የሚለውን ሀሳብም ደግፈዋል።