የአውሮፓ ሀገራት የእስራኤልና ባህሬንን የሰላም ስምምነት አወደሱ
እስራኤል ከሌሎች የዓረብ ሀገራትም ጋር የሰላም ስምምነት ልትፈራረም እንደምትችል ይጠበቃል
ባህሬን የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶችን ተከትላ ከትናንት በስቲያ አርብ እለት ነው ከእስራኤል ጋር የሰላም ስምመነት ላይ የደረሰችው
የአውሮፓ ሀገራት የእስራኤልና ባህሬንን የሰላም ስምምነት አወደሱ
ከሰሞኑ ከተባሩት አረብ ኢሚሬቶች ጋር የሠላም ስምምነት አድርጋ የነበረችው እስራኤል ከባህሬንም ጋር ስምምነት ላይ መድረሷ መካከለኛው ምስራቅን ሰላማዊና የተረጋጋ አካባቢ እንደሚያደርገው የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
ከህብረቱ ባለፈም የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስራኤልና ባህሬን ያደረጉትን የሰላም ስምምነት አድንቀዋል፡፡ ሚኒስትሩ ሄይኮ ማስ የተደረገው የሰላም ውይይትና ስምምነት ቀጣናውን ሰላማዊ ለማድረግ የሚያስችል አንድ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡
የባህሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱላቲፍ አል ዛያኒ እና የእስራኤሉ አቻቸው ጋቢ አሽኬናዚ በስልክ ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡ ሁለቱ ሚኒስትሮች በቀጣናው ሰላምን እና መረጋጋትን ለማምጣት የተደረገው ሰምምነት ከፍተኛ ሚና እንዳለውም መወያየታቸውን ዘ ናሽናል ዘግቧል፡፡
አርብ ዕለት የሰላም ስምምነት ያደረጉት ሁለቱ ሀገራት በቀጣይ አንዳቸው በሌላኛቸው ኤምባሲዎችን እንደሚከፍቱ እና የአውሮፕላን በረራም እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል፡፡
ስምምነቱ የተደረሰበትን ቀን “እውነተኛ ታሪካዊ ቀን” ያሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ እስራኤል እና ባህሬን ሙሉ የዲፕሎማሲ እና የንግድ ግንኙነት መመስረት እንደጀመሩ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ሌሎች የባህረ ሰላጤው ሀገራትም ከእስራኤል ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያድሱ ይጠበቃል፡፡