“አሜሪካ ከእስራኤል ጋር ያላት ግንኙነት በሚያስገርም ሁኔታ ልዩ እንደሆነ ሁሉ ከዩኤኢም ጋር ያላት ወታደራዊ ግንኙነት በጣም ልዩ ነው”-ኩሽነር
ከፍተኛ የአሜሪካ እና የእስራኤል የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሹማምንቶችን የያዘው ልዑክ አቡዳቢ ደርሷል
የትራምፕ ከፍተኛ አማካሪው “ኢራን ተቀዳሚ የቀጣናው ስጋት ነች” ሲሉም ገልጸዋል
የአሜሪካ እና የእስራኤል ከፍተኛ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሹማምንቶችን የያዘው ልዑክ አቡዳቢ ደርሷል
የአሜሪካ እስራኤል ልዑክ አባላትን እየመሩ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ርዕሰ መዲና አቡዳቢ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የደረሱት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ እና አማች ያሬድ ኩሽነር “አሜሪካ ኢራንን እንደተቀዳሚ የቀጣናው ስጋት ታያታለች” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በአየር ማረፊያው ጋዜጣዊ መግለጫን የሰጡት ኩሽነር “አሜሪካ ከእስራኤል ጋር ያላት ግንኙነት በሚያስገርም ሁኔታ ልዩ እንደሆነ ሁሉ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶችም ጋር ያላት ወታደራዊ ግንኙነት በጣም ልዩ ነው” ሲሉ ነው የሃገራቱን ወታደራዊ ግንኙነት በተመለከተ የገለጹት፡፡
የእስራኤል ወታደራዊ አቅም ሊያስከብራት የሚችል ነው ያሉም ሲሆን ከዩኤኢ ጋር ያለንን ወታደራዊ ግንኙነት እናጠናክራለን ብለዋል፡፡
የአሜሪካ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪው ሮበርት ኦብሪያን በበኩላቸው እስራኤልና ዩኤኢ“ከአሜሪካ ጋር በኢራን ላይ አንድ ግንባር ይፈጥራሉ”ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሃገራቱ “እጅግ አስተማማኝ እና ብቁ” የቀጣናው የአሜሪካ አጋሮች መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
አቡዳቢን ከቀጣናው ሳይሆን ከዓለማችን ታላላቅ ከተሞች አንዷ ናት ሲሉም ነው ያሞካሹት፡፡
ለዓመታት ሻክሮ የቆየውን የእስራኤልና የዩኤኢን ግንኙነት “በአብርሃም ስምምነት” ለማለስለስ የተደረገውን ጥረት ያሞካሹም ሲሆን የዩኤኢ ጦር ኃይሎች ምክትል የበላይ አዛዥ እና የአቡዳቢ ልዑል አልጋወራሽ ሞሃመድ ቢን ዛይድን አመስግነዋል፡፡
ከቴልአቪቭ ተነስቶ ታሪካዊ እና የመጀመሪያ የተባለውን የንግድ በረራ ያደረገው ልዑኩ ከፍተኛ የአሜሪካ እና የእስራኤል የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሹማምንቶችን ይዟል መባሉ የሚታወስ ነው፡፡