ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዩኤኢ እና ለእስራኤል የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና የእስራኤል ስምምነት ምን አንደምታ አለው?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተደረሰው ስምምነት የዘውዳዊ ልዑል ሞሀመድ ቢን ዘይድ አል-ናህያንን አመራር አድንቀዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለዩኤኢ እና ለእስራኤል የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና እስራኤል የሀገራቱን ግንኙነት ለማሻሻል እና መደበኛ ግንኙነት ለመጀመር ለደረሱት ቆራጥ ዉሳኔ በኢትዮጵያ መንግስት እና በራሳቸው ስም እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
“እንደዚህ ያሉ ታሪካዊ ውሳኔዎች እና ሰላማዊ ግንኙነትን በድጋሚ ለማስጀመር የተወሰዱት እርምጃዎች ሰላምና መረጋጋትን ለማስጠበቅ በዓለም ዙሪያ ለሚደረጉ ጥረቶች ወሳኝ ናቸው” ብለዋል፡፡
ሁለቱም ሀገራት የኢትዮጵያ የቅርብ ወዳጆች ቢሆኑም በተለይ በኢትዮጵያ የለውጥ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ወዲህ የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች በገንዘብ እና በተለያዩ መንገዶች ኢትዮጵያን በቀዳሚነት በመደገፍ ላይ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡
“ወንድሜን ልዑል ሞሀመድ ቢን ዘይድ አል-ናህያንን ለሚሰጡት አመራር ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “በመካከለኛው ምስራቅ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የተጀመረው ጉዞ እንደሚሳካ እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል፡፡
የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች እና እስራኤል ግንኙነታቸውን ለማደስ ከቀናት በፊት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል፡፡ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ለማደስ ከስምምነት በመድረስ ዩኤኢ 3ኛ የዓረብ ሀገር ነች፡፡ ከዚህ ቀደም ከእስራኤል ጋር መደበኛ ግንኙነት ለመጀመር የተስማሙት የዓረብ ሀገራት ግብጽ እና ዮርዳኖስ ናቸው፡፡
እስራኤል እስካሁን ከገልፍ ሀገራት ጋር መደበኛ ግንኙነት የሌላት ሲሆን አሁን ከዩኤኢ ጋር የተደረሰው ስምምነት ይህን ታሪክ እንደሚቀይረው ይታመናል፡፡
ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እና ዘውዳዊ ልዑል ሞሀመድ ቢን ዘይድ አል-ናህያን
ታሪካዊ የተባለለት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙዎች ቢወደስም ኢራን እና ፍልስጥኤም ግን ኮንነውታል፡፡ በዩኤኢ ክህደት ተፈጽሞብኛል ያለችው ፍልስጥኤም የአቡ ዳቢ አምባሳደሯን እንደምትጠራም ገልጻለች፡፡
ይሁን እንጂ በስምምነቱ ከተደረሱ ነጥቦች አንዱ እስራኤል ዌስት ባንክን ለመጠቅለል የያዘችውን አቋም እንድታዘገይ እና ዉይይት እንዲደረግበት የሚል ነው፡፡
በአሜሪካ የዩኤኢ አምባሳደር ዩሴፍ አል ኦታይባ ከእስራኤል ጋር ያተደረሰው ስምምነት “ለዲፕሎማሲ እና ለአከባቢው ትልቅ ድል ነው” ያሉ ሲሆን አክለውም “በአረብ-እስራኤል ግንኙነት መካከል ውጥረትን የሚቀንስ እና አዎንታዊ ለውጥ ለማምጣት አዲስ ኃይልን የሚፈጥር ነው” ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ የመሩት የሁለቱ ሀገራት ድርድር ዉጤታማ መሆኑ ፣ ሁለቱም የአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ ሀገራት እንደመሆናቸው፤ እንደ አንድ የዲፕሎማሲ ስኬት ታይቶላቸው ለቀጣዩ ምርጫ እንደሚረዳቸው ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁም ቢሆኑ ከሙስና ጋር በተያያዘ የተከፈተባቸውን ክስ ለመቀልበስ አሊያም ለማቅለል ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ይታመናል፡፡
በመጪዎቹ ሳምንታት የእስራኤል እና የዩኤኢ ልዑካኖች ተገናኝተው በኢንቨስትመንት ፣ ቱሪዝም ፣ ቀጥተኛ በረራዎች ፣ ደህንነት ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን ፣ ቴክኖሎጂ ፣ ኢነርጂ ፣ ጤና ፣ ባህል ፣ አካባቢ ፣ አንዳቸው በሌላኛቸው ኤምባሲ ለመክፈት እና ሌሎች የጋራ መስኮች ላይ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሁለቱ የመካከለኛው ምስራቅ በኢኮኖሚ ጠንካራ እና በብዙ ዘርፎች የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙ ማኅበረሰቦች ባለቤት ሀገራት መካከል ቀጥተኛ ትስስር መፍጠር የምጣኔ ሀብት ዕድገትን በማበረታታት ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራን በማጎልበት እና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር አካባቢዉን ለመለወጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የብዙዎች እምነት ነው፡፡
የተሟላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመር ፣ ኤምባሲዎችን ማቋቋም እንዲሁም በእስራኤል እና በዩኤኢ መካከል መደበኛ የንግድ ትስስር መፍጠር በዲፕሎማሲው መስክም ጉልህ ጠቀሜታ የሚኖረው እርምጃ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ስምምነት በሙላት ይፈጸማል? ሌሎች የባህረ ሰላጤው ሀገራት ተመሳሳይ መንገድ ይከተሉ ይሆን? የሚሉት በጊዜ ሂደት የሚመለሱ ጥያቄዎች ናቸው፡፡