አንድ ሲጋራ ማጨስ ከእድሜያችን ላይ ምን ያህል ደቂቃ ይነጥቃል?
የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ አንድ ትንባሆ ማጨስ ከእድሜያችን ላይ በአማካይ 20 ደቂቃን ይቀማል ብሏል
የአለም ጤና ድርጅት ሲጋራ ማጨስ በየአመቱ ከ8 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ህይወት እንደሚቀጥፍ ገልጿል
ሲጋራ ማጨስ ከእድሜያችን ላይ ምን ያህል እንደሚቀንስ የሚጠቁም አዲስ ጥናት ይፋ ሆኗል።
የለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በዛሬው እለት ይፋ ያደረገው ጥናት አንድ ነጠላ ሲጋራ ማጨስ ከአጫሹ እድሜ 17 ደቂቃ እንደሚቀንስ አመላክቷል።
ሴት አጫሽ ስትሆን ደግሞ ወደ 22 ደቂቃ ከፍ እንደሚል አጥኝዎቹ ተናግረዋል።
አዲስ አመት በመጣ ቁጥር ማጨስ አቆማለሁ በሚል ቃል የሚገቡ ሰዎች ማጨስ ምን ያህል እድሜያቸውን እያሳጠረው መሆኑን በመረዳት ለእቅዳቸው ተግባራዊነት ቁርጠኛ እንዲሆኑም አሳስበዋል።
በቀን 10 ሲጋራ የሚያጨሱ ሰዎች ከጥር 1 እስከ 8 ባሉት ሰባት ቀናት ማጨስ ቢያቆሙ 1600 ደቂቃዎችን ወይም ከአንድ ቀን በላይ ከእድሜያቸው ላይ መቀነስን ማስቀረት ይችላሉ ይላል ጥናቱ።
በለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአልኮልና ትንባሆ ጥናት ቡድን መሪ ሳራህ ጃክሰን፥ "ጥናቱ ሲጋራ ማጨስ ምን ያህል አደገኛ መሆኑን በግልጽ ቋንቋ አስቀምጧል፤ ማጨስ ማቆም ጤናን አሻሽሎ በአጭር ከመቀጨት እንደሚታደግ አመላክቷል" ብለዋል።
የብሪታንያ ብሄራዊ ስታስቲክስ ተቋም መረጃ እንደሚያሳየው በ2023 እድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆኑ 6 ሚሊየን ሰዎች ያጨሳሉ።
ሲጋራ ማጨስ በእንግሊዝ "ሊቀረፍ ከሚችል ሞት" ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ በመያዝ በየአመቱ ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት እንደሚቀጥፍ መጥቀሱን ሚረር ዘግቧል።
የአለም ጤና ድርጅት ባለፈው አመት ያወጣው መረጃም በሲጋራ ማጨስ ምንክያት በየአመቱ ከ8 ሚሊየን በላይ ሰዎች ህይወት እንደሚያልፍ ማመላክቱ ይታወሳል።
ከ1 ነጥብ 3 ሚሊየን በላይ የማያጨሱ ሰዎችም ለሚያጨሱ ሰዎች ባላቸው ቅርበት ምክንያት እንደሚሞቱ ድርጅቱ አስታውቋል።
ከአለማችን ትንባሆ አጫሾች 80 በመቶዎቹ በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት የሚኖሩ ናቸው።
የ2020 የአለም ጤና ድርጅት ጥናት 22 ነጥብ 3 በመቶ የአለማችን ህዝብ ሲጋራ አጫሽ መሆኑን ማመላከቱ አይዘነጋም።