አውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ የጣለውን ከባድ ማዕቀብ እስከ ጥር 2023 አራዘመ
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን “ሞስኮ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሏን መቀጠል አለባት”ብሏል
ጆሴፕ ቦሬል “ከፑቲን እና ከክሬምሊን ጋር ቅርበት ያላቸውን አካላትን ዒላማ ማድረጉ እንቀጥልበታለን” ብለዋል
አውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ የጣለውን ከባድ ማዕቀብ እስከ ጥር 2023 ማራዘሙን አስታወቀ፡፡
የአውሮፓ ህብረት ስድስት ሰፊ እና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ማእቀቦች ውጤታማነት ለመጠበቅ እና ለማጠናከር አዳዲስ የማዕቀብ እርምጃዎች ለመሰውሰድ በሚያስችሉት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የጋራ ሃሳብ ላይ ደርሷል፡፡
በዚህም ህብረቱ፤ በሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ አዳዲስ ማዕቀቦች ተጨምረውበት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና እንዲራዘም ከሚል ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን “ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገው ጦርነት ያለማቋረጥ ቀጥሏል፤ ስለዚህ እኛ ዛሬ የምናቀርበው ጠንካራ የአውሮፓ ህብረት ማዕቀብ በክሬምሊን ላይ እንዲጠናከር፣ የበለጠ እንዲተገበር እና እስከ ጥር 2023 እንዲራዘም ነው” ብለዋል፡፡
ሞስኮ ለጥቃቱ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን መቀጠል አለባት ሲሉም የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል በበኩላቸው “የአውሮፓ ህብረት ማዕቀቦች ጠንካራ እና ከባድ ናቸው፤ ከፑቲን እና ከክሬምሊን ጋር ቅርበት ያላቸውን አካላትን ዒላማ ማድረጉ እንቀጥልበታለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የዛሬው ማዕቀብ የቡድን-7 አባል ሀገራትን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ያለንን የተቀናጀ አካሄድ ያንጸባርቃል ያሉት ቦሬል፤ ከእነዚህ እርምጃዎች በተጨማሪ የንብረትም ሆነ የጉዞ እግድ ሊደረግባቸው የሚገቡ አካላት ካሉ ለምክር ቤቱ ሃሳብ አቀርባለሁ ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የወሰነው ማዕቀብ የላቀ የቴክኖሎጂ ኤክስፖርት ቁጥጥርን በማጠናከር በሩሲያ ወርቅ ላይ እገዳ የሚጥል መሆኑም አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ የአውሮፓ ህብረት ማዕቀብ በምንም መልኩ በሶስተኛ ሀገራት እና በሩሲያ መካከል ያለውን የግብርና ምርቶች ግብይት አይመለከትም ብለዋል ቦሬል፡፡