ሃንጋሪ፤ የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ጉዳይ ላይ የሚያጠበቅውን ነገር እንዲያቆም ጠየቀች
በብራሰልስ በመካሄድ ላይ ባለው የህብረቱ ጉባዔ ምናልባትም ተጨማሪ ማዕቀቦች ሊጣሉ እንደሚችሉ ተነግሯል
ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ነገሮችን እያባባሱ ነው ብለዋል
ሃንጋሪ የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ጉዳይ ላይ የሚያጠበቅውን ነገር እንዲያቆም ጠየቀች፡፡
ቡዳፔስት በአውሮፓ ያለው የኑሮ ሁኔታ እየከፋ ነው በሚል ህብረቱ በሩሲያ ላይ ለመጣል የሚያስባቸውን ሌሎች ማዕቀቦች ተቃውማለች፡፡
የቅጣት እርምጃዎቹ ከአሁን በኋላ የአውሮፓውያንን ኑሮ ከማወሳሰብ የዘለለ ፋይዳ ሊኖራቸው እንደማይችልም ገልጻለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን በሩሲያ ላይ ጫናን ለማብዛት በሚል ለ7ኛ ዙር ማዕቀቦችን ለመጣል በዩክሬን እና በአንዳንድ የህብረቱ አባል ሃገራት የቀረበውን ጥሪ ተቃውመዋል፡፡
ኦርባን ማዕቀቦቹ ልክ እንደ ጦርነቱ ሁሉ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስን እየፈጠሩ ነው ብለዋል፡፡
ሰላም እንፈልጋለን አዎ ነገር ግን ከዚህ በላይ የሚጣሉ ተጨማሪ ማዕቀቦችን አንፈልግም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
ሆኖም ሩሲያ በዩክሬን ላደረገችው ወረራ መቀጣት ብቻም ሳይሆን መዳከም ጭምር አለባት የሚሉ የእርምጃው ደጋፊዎች አሁንም ማዕቀቦች እንዲጣሉ ይፈልጋሉ፡፡ ከነዳጅ እና ከሌሎችም ምርቶች የምታገኘውን ገቢ በማሳጣት ጫናው እንዲሰማት ይገባል ባይም ናቸው፡፡
ዛሬን ጨምሮ በብራሰልስ በመካሄድ ላይ ባለው የህብረቱ ጉባዔ ምናልባትም ተጨማሪ ማዕቀቦች ሊጣሉና ከአሁን ቀደም የተጣሉት ለተጨማሪ 6 ወራት ሊራዘሙ እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡ ሆኖም ማዕቀቦቹ በአውሮፓ ያለውን የዋጋ ግሽበት በጥቅሉም የኑሩ ውድነት ሁኔታ ይበልጥ እያባባሱት ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ ይህም በህብረቱ አባላት መካከል ልዩነትን የፈጠረ እንደሆነም ነው የሚነገረው፡፡
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ይህ የምዕራባውያን እሳቤ የታሰበውን ያህል ውጤት እንዳላመጣ ከሰሞኑ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ፑቲን የሩሲያ የንግድ ግንኙነት ወደ ብሪክስ አባል ሃገራት እየዞረ መምጣቱን በቡድኑ ጉባኤ ላይ መናገራቸውም የሚታወስ ነው፡፡