የቡድን ሰባት ሀገራት በሩሲያ ነዳጅ ላይ የመሸጫ ጣሪያ አወጡ
ሩሲያ የቡድን ሰባት ሀገራት ካስቀመጡት የመሸጫ ጣሪያ በላይ ነዳጅ በባህር አጓጉዛ እንዳትሸጥም እገዳ ጥለዋል
ሩሲያ እስካሁን በቡድን ሰባት አባል ሀገራት ስለተጣለባት ተመን ምላሽ አልሰጠችም
የቡድን ሰባት ሀገራት በሩሲያ ነዳጅ ላይ የመሸጫ ጣሪያ አወጡ።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ስድስት ወራት ያለፉት ሲሆን ጦርነቱ በዓለም ምግብ እና ነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል።
ይህ በዚህ እንዳለም ጦርነቱ በዓለም ዲፕሎማሲ ላይ የተለያዩ መፋለሶችን ያስከተለ ሲሆን ሀገራት ከትብብር ይልቅ ጎራ ለይተው እንዲሰለፉ እያደረገም ይገኛል።
አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ላይ በተለያየ መንገድ በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ በሩሲያ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦችን ጥለዋል።
ሩሲያም የአጸፋ እርምጃ በመውሰድ ላይ ስትሆን ማዕቀቡ ለአውሮፓ ሀገራት የምታቀርበውን ጋዝ ሽያጭ እክል አስከትሏል።
ይሄንን ተከትሎም 40 በመቶ ለሚሆኑ የአውሮፓ ሀገራት ነዳጅ ስታቀርብ የነበረችው ሩሲያ በማዕቀቡ ምክንያት ለአውሮፓውያን ነዳጅ መላክ አለመቻሏን በተደጋጋሚ ገልጻለች።
በነዳጅ ዕጥረት እየተፈተነ ያለው የአውሮፓ ህብረትም በሩሲያ ላይ የጣለውን ማእቀብ እስከማላላት ቢደርስም ሞስኮ ነዳጇን በሚፈለገው ልክ አለመላኳን ሮይተርስ ዘግቧል።
የአውሮፓ ባለ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑት ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ቤልጂየም እና ሌሎች ሀገራት በነዳጅ ዕጥረት እየተፈተኑ ናቸው ተብሏል።
እነዚህ ሀገራት ሩሲያ ነዳጇን እንደጦር መሳሪያ እየተጠቀመችበት ነው ሲሉም ሞስኮን ከሰዋል።
አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን ጣልያን እና ካናዳ ስብስብ የሆነው የቡድን ሰባት ሀገራት የፋይናንስ ሚንስትሮች በሩሲያ ነዳጅ ላይ የዋጋ ተመን አውጥተዋል።
ሀገራቱ የሩሲያ ነዳጅ በሀይል እጥረት እየተፈተኑ ላሉ የአውሮፓ ሀገራት በተቀመጠው የመሸጫ ተመን ሊደርስ ይገባል ሲሉ ወስነዋል ተብሏል።
ይሁንና እነዚህ ሀገራት ሩሲያ በምን ያህል የገንዘብ መጠን ልትሸጥ እንደሚገባ የዋጋ ተመን ቁጥሩን አላሳወቁም።
ሩሲያ በበኩሏ እስካሁን በቡድን ሰባት አባል ሀገራት ስለወሰኑት የነዳጅ ሙሸጫ ዋጋ ተመን በይፋ ያለችው ነገር የለም።
እንደ ቡድን ሰባት አባል ሀገራት ውሳኔ ከሆነ ሩሲያ ነዳጇን ከተተመነው የመሸጫ ዋጋ ውጪ በባህር አጓጉዛ መሸጥ አትችልም።