ዶናልድ ትራምፕ፤ “በተጭበረበረ ምርጫ” መሸነፋቸውን በድጋሚ ተናገሩ
በመድረኩ በስደተኞችና ተያያዥ ፖሊሲዎቻቸው ፕሬዝዳንት ባይደንን የተቹት ትራምፕ በቀጣይ ለፕሬዚዳንትነት ስለመወዳራቸው የተናገሩት ነገር
ትራምፕ የተናገሩት የቀድሞውን ረዳታቸውን ወግ አጥባቂውን የኮንግረስ እጩ ማክስ ሚለርን ለመደገፍ በተገኙበት የምርጫ ቅስቀሳ መሰል መድረክ ላይ ነው
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ከኋይት ሃውስ ከወጡ በኋላ ለመጀመሪ ጊዜ፤ ሕዳር ወር ላይ ተካሂዶ የነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተጭበርብሮ እንደነበር ገለጹ፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ በፊትም ምርጫው እንደተጭበረበረ ሲገልጹ የነበረ ቢሆንም ከቤተ መንግስት ከወጡ በኋላም ግን ይህንኑ ቅሬታ ለመጀመሪ ጊዜ አሰምተዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት፤ ከቤተ መንግስት ከወጡ በኋላ የመጀመሪያ ንግግር አድርገዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ፤ በኦሃዩ ባደረጉት ንግግር የሕዳሩ ምርጫ በመጭበርበሩ ምክንያት ለሽንፈት እንደተዳረጉ ገልጸዋል፡፡
ተካሂዶ የነበረውን ምርጫ ማሸነፋቸውን የገለጹት ትራምፕ፤ ወደፊት “እናሸንፋለን” በማለት ተናግረዋል ነው የተባለው፡፡
ዶናልድ ትራምፕና ፓርቲያቸው ከምርጫው ጋር ተያይዞ ከ 60 በላይ የፍርድ ቤት አቤቱታዎችን አቅርበው የነበረ ቢሆንም ጥያቄዎቹ ግን ውድቅ መደረጋቸው ይታወሳል፡፡
“ምርጫውን ሁለት ጊዜ አሸንፈናል፣ ለሶስተኛ ጊዜ ደግሞ እናሸንፋለን” የሚል የተስፋ ንግግር ማድረጋቸውን የጀርመን ድምጽ የእንግሊዝኛው አገልግሎት ዘግቧል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት፤ ምርጫው ተጭበርብሮ እንደነበር ከመግለጽም ባለፈ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ወደ አሜሪካ የገቡ በርካታ ስደተኞችን ማንነትና ተያያዥ ጉዳዮችን በሚገባ መያዝ አልቻሉም በማለት ተችተዋቸዋል፡፡
አሜሪካ በጆ ባይደን ዘመን በዓለም ላይ ያላት ሚና ዝቅተኛ እንደሆነ ያነሱት ዶናልድ ትራምፕ፤ የአሁኑ አስተዳደር “ለቻይና ያጎበደደ ነው” ብለዋል፡፡
ትራምፕ በኦሃዮ ባደረጉት ንግግር ደጋፊዎቻቸው ቀስቅሰውት በነበረው የካፒቶል ሂል አመጽ መከሰሳቸውን የደገፉ የፓርቲያቸውን (ሪፐብሊካን) አባላት ክፉኛ ተችተዋል፡፡
በተለይ ክሱን ደግፎ የነበረውን የኦሃዮን የሪፐብሊካን ተወካዮ አንቶኒ ጎንዛሌዝን ክፉኛ ተችተዋል፡፡
በአንጻሩ ጎንዛሌዝን በመፎካከር ኦሃዮን በኮንግረስ ለመወከል የሚወዳደሩትን ወግ አጥባቂውን እጩ ማክስ ሚለርን አሞግሰዋል፡፡
የኮንግረስ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫው በመጪው ህዳር በ50ውም የሃገሪቱ ግዛቶች የሚካሄድ ነው፡፡
ሚለር በ2016ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ አጋር ነበሩ፡፡
ትራምፕ ሚለርን ምረጡ ለማለት በተገኙበት በዚህ ቅስቀሳ መሰል የንግግር መድረክ በቀጣይ ለፕሬዚዳንትነት ይወዳደሩ እንደሆነ በግልጽ እንዳልተናገሩም የዜና ምንጩ ጠቅሷል፡፡
ይሁንና በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው የመካከለኛ ጊዜ ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ በሁለቱም ምክር ቤቶች ውስጥ አብላጫ ድምጽ እንደሚያገኝ ተናግረዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ፤ በምርጫው እንዳሸነፉ በመግለጽ፤ ከኋይት ሃውስም ሊወጡ እንደማይችሉ ሲናገሩ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁን ደግሞ፤ "እኛ ሪፐብሊካኖች ሴኔቱንም እና ኮንግረንሱንም እንቆጣጠረዋለን " ማታቸው ተጠቅሷል፡፡