በባንኮች 1 ዶላር በስንት ብር እየተመነዘረ ነው?
የግል ንግድ ባንኮች ለ1 ዶላር ከ117 እስከ 121 ብር መግዣ፤ ከ119 እስከ 123 ብር መሸጫ ዋጋ አውጥተዋል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1 ዶላርን በ113 ብር ገዝቶ በ115 ብር እየሸጠ ነው
ብሔራዊ ባንክ ከሰሞኑ የውጭ ምንዛሪ መግዣና መሸጫ መሃል ያለው ልዩነት እንዲቀራረብ ባሳሰበ ማግስት የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ለውጥ ታይቷል።
ባንኮች በውጭ ምንዛሬ መሸጫ ዋጋቸው ላይ ካደረጉት ቅናሽ ባሻገር በመግዣ ዋጋቸውም ላይ ከ10 ብር በላይ ጭማሪ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ጥቅምት 13 2017 ዓ.ም የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ የባለፈው ሳምንት ተመን አስቀጥሏል።
በዚህም አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ113.1308 ብር እየገዛ ሲሆን፤ በ115.3934 ብር እየሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
ኦሮሚያ ባንክ ዛሬም ከፍተኛውን የዶላር መግዣ ዋጋ አቅርቧል። ባንኩ የጥቅምት 12 2017 ዓ.ም እለታዊ የምንዛሬ ተመኑን ይፋ ሲያደርግ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ121.3066 ብር እየገዛ በ123.7327 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው ያስታወቀው።
ዳሽን ባንክ ደግሞ የትናንቱን ተመን አስቀጥሎ አንድ ዶላርን በ119.2027 ብር እየገዛ መሆኑን ገልጿል። 121.5868 ብር የባንኩ የዶላር መሸጫ ዋጋ ነው።
ንብ ባንክ ባወጣው እለታዊ የውጭ ምንዛሬ ተመን አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ117.1502 ብር ገዝቶ በ119.4932 ብር እየሸጠ መሆኑን ይፋ አድርጓል።