እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ ከሄዝቦላ ጋር ግንኙነት ባላቸው የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጥቃት ፈጸመች
የእስራኤል ጦር እንገደለፈው አል-ቃርድ አል-ሀሰን ማህበር ላይ ጥቃት ፈጽሟል
ከእስራኤል በድንበር አካባቢ ለአንድ አመት ያህል የተኩስ ልውውጥ ካደረገች በኋላ ነው በሄዝቦላ ላይ የተጠናከረ የአየር እና የእግረኛ ጦር ጥቃት የፈጸመችው
እስራኤል ሊባኖስ ውስጥ ከሄዝቦላ ጋር ግንኙነት ባላቸው የፋይናንስ ተቋማት ላይ ጥቃት ፈጸመች።
እስራኤል በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ደቡባዊ ዳርቻ እንዲሁም በደቡብ እና ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል በሚገኙ ከሄዝቦላ ጋር ግንኙነት ባላቸው የፋይናንስ ተቋማት ቅርንጫፎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን ገልጻለች።
ባለፈው እሁድ ሰዎች ከጥቃቱ ለመዳን ያስችለናል ወዳሉት ቦታ ለመሄድ በሚሞክሩበት ወቅት ከፍተኛ ትርምስ ተከስቶ ነበር።
የእስራኤል ጦር እንገደለፈው አል-ቃርድ አል-ሀሰን ማህበር ላይ ጥቃት ፈጽሟል። ማህበሩ በአካባቢው ላለው ማህበረሰብ የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም እስራኤል እና አሜሪካ ግን በኢራን ለሚደገፈው ሄዝቦላህ ድጋፍ በመስጠት ይከሱታል።
ሄዝቦላ በዚህ ጉዳይ በይፋ ያለው ነገር የለም።
ይህ ጥቃት እስራኤል በቡድኑ ጥቅም ላይ ከሚውሉት መሰረተልማቶች ባሻገር ጦርነቱን የማስፋፋት ፍላጎት እንዳላት ያሳያል ተብሏል። ጥቃቱ የተፈጸመው የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይጀን የመካከለኛው ምስራቅ ልዩ መልእክተኛ ጦርነቱን በድርድር መቋጨት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎችን ለማየት ቤሩት ከመድረሳቸው ከሰአታት በፊት ነው።
ከእስራኤል በድንበር አካባቢ የአንድ አመት ያህል የተኩስ ልውውጥ ካደረገች ከአንድ አመት በኋላ ነው በሄዝቦላ ላይ የተጠናከረ የአየር እና የእግረኛ ጦር ወረራ የፈጸመችው። ሄዝቦላ ወደ እስራኤል መተኮስ የጀመረው ባለፈው አመት ጥቅምት 8 ሲሆን ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ለገባው የ
ለፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ አጋርነት ለማሳየት ነበር።
እስራኤል በሄዝቦላ ላይ የአየር እና የመሬት ጥቃት የከፈተችው ጥቃት ሸሽተው የተፈናቁሉ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የሰሜን እስራኤል ነዋሪዎችን ወደ ቦታቸው ለመመለስ መሆኑን ገልጻለች።
በአል-ቃርድ አል-ሀሰን ማህበር ላይ ጥቃት የተፈጸመው፣ የእስራኤል ጦር ለቃችሁ ውጡ የሚል ማስጠንቀቂያ ከስተላለፈ ከ20 ደቂቃ በኋላ ነው።
የሊባኖስ ብሔራዊ ዜና አገልግሎት(ኤንኤንኤ) እንደዘገበው ከሆነ በደቡባዊ ቤይሩት ዳሂህ 11 ጥቃቶች ተፈጽመዋል። በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጨው ቪዲዮ እንደሚያሳየው ከሆነ አገልግሎት እየሰጠ ካለው የሊባኖስ ኤየርፖርት 500 ሜትር ርቀት ላይ በላይላኪ አካባቢ አንድ የአል ቃርድ አል ሀሰን ቅርጫፍ ወድሟል።
ሌላ ቪዲዮ ደግሞ የዚህ ማህበር ቅርጫፍ ያለበት ህንጻ መፈራረሱን አሳይቷል።
የዜና አገልግሎቱ አክሎም የአየር ጥቃቱ ሄዝቦላ ከፍተኛ ይዞታ ባለባቸው ነበቲህ፣ ታይሬ፣ በደቡብ ሊባኖስ በሸሀቢህ እንዲሁም በምስራቅ ቤካ ሸለቆ በሚገኙት ባልቤክ፣ ሄርሜል እና ራያክ ከተሞች ያሉ ቅርንጫፎችን መትቷል።
እስራኤል በሊባኖስ ባደረገችው መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት በቀጣናው የኢራን ጠንካራ አጋር የሆነውን የሄዝቦላ ታጣቂ ቡድን መሪ ሀሰን ነስረላህን ገድላለች።