ከጋዛው ጦርነት መጀመር በኋላ ሀማስ 15 ሺህ አዳዲስ ታጣቂዎችን መመልመሉን የአሜሪካ ደህንንት መረጃ አመላከተ
በጦርነቱ ቡድኑ ካሉት 25 ሺህ ታጣቂዎች 20 ሺህ የሚጠጉት መገደላቸው መነገሩ ይታወሳል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/1/25/243-120525-img-20250125-110219-759_700x400.jpg)
እስራል በበኩሏ ሀማስ የመለመላቸውን ታጣቂዎች “የሚያስለጥንበት ስፍራም ሆነ የሚያስታጥቀው ትጥቅ የለውም” ብላለች
የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሀማስ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ10 -15 ሺ የሚደርሱ አባላትን መመልመሉ ተነግሯል፡፡
ሃማስ አዳዲስ አባላትን በተሳካ ሁኔታ መመልመል ቢችልም ብዙዎቹ ወጣት እና ያልሰለጠኑ እንዲሁም በቀላል የጥበቃ ተልዕኮዎች ላይ የሚሰማሩ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ ደህንነት ተቋም ማብራርያ የተደረገላቸው ሁለት የኮንግረስ ምንጮች ለሮይተርስ እንደገለጹት በኢራን የሚደገፈው ቡድን ለእስራኤል ስጋት ሆኖ ሊቀጥል ይችላል፡፡
በመረጃው መሰረት በዚህ ወቅት ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው የሃማስ ተዋጊዎች መገደላቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሃማስ በፍልስጤም ግዛት የሞቱበትን ያህል አዳዲስ ታጣቂዎችን እንደመለመለ ይህም ቀጣይ ለሚሰነዝራቸው ጥቃቶች እና በጋዛ ጠንካራ ሆኖ ለመዝለቅ ወሳኝ መሆኑን ከሳምንት በፊት ተናግረው ነበር፡፡
ሚኒስትሩ "እስራኤል በተለያዩ የጋዛ ክፍሎች ወታደራዊ ዘመቻዎችን አጠናቃ ወደ ኋላ በተመለሰች ቁጥር የሃማስ ታጣቂዎች እንደገና በመደራጀት የተፈጠረባቸውን ክፍተት ለመሙላት አዳዲስ ታጣቂዎችን ከመመልመል ወደ ኋላ ብለው አያውቁም" ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ቀደም እስራኤል ባወጣችው ሪፖርት ሀማስ ከያዛቸው 25 ሺህ የሚደርሱ ታጣቂዎች መካከል 20 ሺ የሚሆኑት በጦርነቱ መገደላቸውን ይፋ እድርጋ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሮይተርስ በዘገባው በሃማስ ትክክለኛ የታጣቂዎች ቁጥር ዙሪያ መረጃ መሰብሰብ ከባድ እንደሆነ ነገር ግን ከጥቅምት ሰባቱ ጥቃት በፊት ከ20 – 25 ሺህ ተዋጊዎች እንደነበረው የአሜሪካ ደህንነት መረጃ ማመላከቱን ጠቅሷል፡፡
የተኩስ አቁም ስምምነቱ ከተጀመረ በነበሩት ተከታታይ ቀናት ሀማስ በጋዛ ውስጥ ጠንካራ አቅም እንዳላው ለመሳየት በፍጥነት ተንቀሳቅሷል፡፡
በሀማስ የሚመራው የጋዛ አስተዳደር የጸጥታ ርምጃዎችን እንደገና ለማስጀመር እና መሰረታዊ አገልግሎቶችን ወደ ስራ ለመመለስ እየሰራ ይገኛል፡፡
በተመድ የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን በሀማስ አዲስ ምልምሎች ዙሪያ በሰጡት አስተያየት "ሀማስ ወጣቶችን እንደሚመለምል እናውቃለን፤ ነገር ግን ወጣቶችን ቢመለምሉም መሳሪያም ሆነ ማሰልጠኛ ቦታ የላቸውም፤ እነዚህን ወጣቶች በእስራኤል ላይ ማነሳሳት ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን አሸባሪ መሆን አይችሉም ምክንያቱም ቡድኑ መሳሪያም ሆነ ሮኬቶችን ማስታጠቅ አይችልም " ብለዋል፡፡
በቀጣይዙር ለመደራደር በጣም አስቸጋሪ ከሚሆኑ ጉዳዮች አንዱ ከጦርነቱ በኋላ የጋዛ አስተዳደር እንዴት ይሆን የሚለው ነው፤ እስራኤል ከድሕረ ጦርነት በኋላ የሃማስ በስልጣን ላይ መቆየትን እንደማትቀበል ተናግራለች፡፡
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ማይክ ዋልትዝ “ሀማስ በፍፁም ጋዛን አያስተዳድርም በዚህ የማይስማማ ከሆነ ዋሽንግተን እስራኤልን ማድረግ ያለባትን እንድታደርግ ትደግፋለች” ብለዋል።