በጋዛው ጦርነት የተሳተፉ የእስራኤል ወታደሮች በውጭ ሀገራት ለእስር መጋለጣቸው ተነገረ
እስራኤል በበኩሏ በወታደሮቹ ላይ ለክስ የሚያበቃ ማስረጃ ሳይኖር ማንኛውም ሀገር ሊያስራቸው አይገባም ብላለች
ወታደሮቹ በጋዛው ጦርነት በዘር ማጥፋት ወንጀል ተሳትፈዋል በሚል ነው ለእስር ተጋልጠዋል የተባለው
በብራዚል በዕረፍት ላይ የነበረ እስራኤላዊ ወታደር በጋዛ እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት የጦር ወንጀሎች ተጠያቂ ነው የሚል ክስ ከቀረበበት በኋላ በፍጥነት ሀገሪቱን ለቆ ወጥቷል፡፡
ክሱ የቀረበው በጋዛ ውስጥ የሚያገለግሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእስራኤል ወታደሮችን እንቅስቃሴ በመከታተል ክሶችን በሚያቀርበው ሂንድ ራጃብ ፋውንዴሽን (ኤችአርኤፍ) ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት ብራዚላዊ ዳኛ ኤችአርኤፍ ወታደሩ በጋዛ ሲቪል ቤቶችን በማፍረስ ላይ ተሳትፏል በሚል ባቀረበው ክስ መሰረት ፖሊስ ወታደሩን እንዲመረምር ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።
በጋዛው ጦርነት በወላጆቿ መኪና ውስጥ እያለች ከእስራኤል ታንኮች በተወነጨፈ ተኩስ ህይወቷ ያለፈው ሂንድ ራጃብ ስም የተቋቋመው ለፍልስጤም ውግንና ያለው የህግ ፋውንዴሽን ነው፡፡
መቀመጫውን ቤልጅየም ያደረገው ተቋም የእስራኤል ወታደሮች ተሳትፈውባቸዋል ያላቸውን የጦር ወንጀሎች የሚያመላክቱ 1ሺህ የቪዲዮ እና የድምጽ ሪፖርቶችን፣ የፎረንሲክ ትንተናዎችን እና ሌሎች ሰነዶችን ለአለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ማቅረቡን ተናግሯል።
እስራኤል በጋዛ የጦር ወንጀሎች ተፈጽመዋል በሚል የውጭ ሀገራት ፍርድ ቤቶች በእስራኤላውያን ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ቡድኖች ግፊት እያደረጉ ቢሆንም ድርጊቱ "የፕሮፓጋንዳ እንቅስቃሴ ነው" በማለት አውግዛለች፡፡
አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና በቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት እንዲሁም የሃማስ መሪ ኢብራሂም አል-ማስሪ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል የእስር ማዘዣ አውጥቷል።
የፍርድ ቤት ማዘዣው በእስራኤል ውስጥ ቁጣን የቀሰቀሰ ቢሆንም በጋዛ ወታደራዊ አገልግሎት በሰጡ እስራኤላውያን ላይ ተመሳሳይ ማዘዣ ሊወጣ ይችላል የሚል ስጋትም ፈጥሯል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “የክስ ሂደቱ ውጤት ሊያመጣ የማይችል ፣ በጠንካራ ማስረጃ ያልተደገፈ እና ከአሸባሪ ድርጅቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባላቸው አካላት የሚፈጸም መሆኑን እናውቃለን” ብሏል፡፡
ሂንድ ራጃብ ፋውንዴሽን (ኤችአርኤፍ) በበኩሉ “እስራኤል በፍልስጤማውያን ላይ የፈጸመቸው የጦር ወንጀል በዝምታ እንዳይታለፍ” እና የሀገሪቱን ወታደሮች እየተከታተለ ፍትህ ለማግኝት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡