ቲክቶክ በአሜሪካ ያቋረጠውን አገልግሎት በመመለስ ሂደት ላይ ነው፤ ትራምፕን አመስግኗል
ቲክቶክ ከብሔራዊ ደህንነት ጋር በተያያዘ ምክንያት እንዲዘጋ የሚያዘው ህግ እሁድ እለት ተግባራዊ ከመሆኑ ቀደም ብሎ ቅዳሜ ምሽት ላይ ነበር አገልግሎቱን ያቋረጠው

ትራምፕ ቲክቶክን በተመለከተ እያራመዱ ያሉት አቋም በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ከያዙት አቆም ጋር የሚቃረን ነው ተብሏል
ቲክቶክ ያቋረጠውን አገልግሎት በመመለስ ሂደት ነው፣ ትራምፕን አመስግኗል።
ታዋቂ የአጫጭር ቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያ ቲክቶክ ፕሬዝደንት ትራሞፕ በዛሬው እለት ወደ ቢሮ ሲገቡ መተግበሪያ በአሜሪካ እንዲሰራ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ተከትሎ አቋርጦነት የነበረውን አገልግሎት በመመለስ ላይ እንደሚገኝ ሮይተርስ ዘግቧል።
"ግልጹን ለመናገር ምርጫ የለንም። ማዳን አለብን" ሲሉ በትናንትናው እለት ባደረጉት የቅደመ-በዓለ ሲመት ንግግር የገለጹት ትራምፕ አሜሪካ 170 ሚሊዮን ዜጎቿ የተጠቃሚ የሆኑበትን መተግበሪያ ለመመለስ የባለቤትነት ድርሻ እንደምትፈልግ አክለዋል።
ከእሁድ ምሽት ጀምሮ የቲክቶክ መተግበሪያን ከአሜሪካ ስቶሮች ማውረድ ቆሟል።
"ከአገልግሎት ሰጭዎቻችን ጋር በተደረገ ስምምነት ቲክቶክ አገልግሎቱን በመመለስ ሂደት ላይ ነው"ሲል ቲክቶክ ተመራጩን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባመሰገነበት መግለጫው ገልጿል።
ቲክቶክ ለትራምፕ ምስጋና ያቀረበው በዓለ ሲመታቸውን ሊፈጽሙ አንድ ቀን ሲቀራቸውና የአሜሪካ-ቻይና ግንኙነት ውጥረት ውስጥ በገባበት ወቅት ነው። ትራምፕ በቻይና ላይ ተጨማሪ ታሪፍ እንደሚጥሉ የገለጹ ቢሆንም ከቻይናው መሪ ጋር ተጨማሪ ቀጥተኛው ንግግር የማድረግ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
በአሜሪካ የቻይና ኢምባሲ ባለፈው አርብ እለት አሜሪካ ፍትሃዊ ያልሆነ የመንግስት ሰልጣን ተጠቅማ ቲክቶክ እንዳይሰራ አድርጋለች ሲል ባለፈው አርብ ከሷል።
"ቻይና ህጋዊ መብቷን እና ፍላጎቶቿን ለማስጠበቅ ሁሉንም እርምጃዎች ትወስዳለች" ብለዋል የኢምባሲው ቃል አቀባይ።
ቲክቶክ ከብሔራዊ ደህንነት ጋር በተያያዘ ምክንያት እንዲዘጋ የሚያዘው ህግ እሁድ እለት ተግባራዊ ከመሆኑ ቀደም ብሎ ቅዳሜ ምሽት ላይ ነበር አገልግሎቱን ያቋረጠው።
ትራምፕ ቲክቶክ በአሜሪካ ያለውን ተደራሽነት እንዲያቆም ወይም እንዲሸጥ የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ጊዜውን በማራዘም የአሜሪካን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ግልጽ አድርገዋል።
"አሜሪካ 50 በመቶ የቲክቶክ ድርሻ እንዲኖራት ትፈልጋለች" ብለዋል ትራምፕ ትሩዝ በተባለው ማህበራዊ ገጻቸው።
ትራምፕ እንዳሉት የሚያሳልፉት ውሳኔ ቲክቶክ አሜሪካ ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጥ በሚያደርጉ ኩባንያዎች ላይ ተጠያቂነት እንደማያስከትል ግልጽ ያደርጋል።
ትራምፕ ቀደም ብለው ወደ ቢሮ ከገቡ በኋላ ቲክቶክን ለ90 ቀናት ሊያራዝሙ እንደሚችሉ ተናግረው ነበር።
ንብረትነቱ የቻይናው ባይቲዳንስ የሆነው ቲክ ቶክ በመጨረሻው ሰአት ለተጠቃሚዎቹ ባስቀመጠው መልእክት "ቲክ ቶክን የሚያግደው ህግ በአሜሪካ ጸድቋል። ይህ ማለት እንዳለመታል ሆኖ ከአሁን በኋላ ቲክቶክን መጠቀም አትችሉም ማለት ነው። ፕሬዝደንት ትራምፕ ቢሮ ሲገቡ ቲክቶክን እንደሚመልሱ በማመላከታቸው እድለኞች ነን። ነቅታችሁ ጠብቁን" ብሎ ነበር።
የቪዲዮ አርትኦት መስሪያው ካፕከትና ሌሞን8 ጨምሮ ሌሎች የባይቲዳንስ መተግበሪያዎች ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ አሜሪካ ውስጥ ከአፕስቶር እንደወረዱ ናቸው።
ትራምፕ ቲክቶክን በተመለከተ እያራመዱ ያሉት አቋም በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው ከያዙት አቆም ጋር የሚቃረን ነው ተብሏል።