በ2023 በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር ከ2015 ወዲህ ከፍተኛው መሆኑ ተነገረ
በኢራን ባለፈው አመት 853 ሰዎች በሞት መቀጣታቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያሳያል

ቻይና፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ሶማሊያ እና አሜሪካ ከፍተኛ የሞት ቅጣት የተመዘገበባቸው ሀገራት ናቸው
በ2023 በአለማቀፍ ደረጃ የተፈጸመው የሞት ቅጣት ከ2015 ወዲህ ከፍተኛው መሆኑን አለማቀፉ የመብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ።
አምነስቲ በዛሬው እለት ይፋ ባደረገው ሪፖርት ባለፈው የፈረንጆቹ አመት በ16 ሀገራት 1 ሺህ 153 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል ብሏል፤ ይህም ከ2022 በ30 በመቶ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን በመጥቀስ።
አሃዙ በሺዎች በሞት ይቀጡባታል ተብላ የምትጠበቀውን ቻይና በመረጃ እጥረት ምክንያት ማካተት አለመቻሉንም አብራርቷል።
እንደ አምነስቲ ሪፖርት ከሆነ በኢራን በ2023 853 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል፤ አሃዙ በ2022 ከተፈጸመው በ277 ብልጫ ያለው መሆኑንም ጠቅሷል።
በኢራን በሞት ከተቀጡት ውስጥ 24 ሴቶችና ወንጀል ሲፈጽሙ ህጻን የነበሩ አምስት ሰዎች ይገኙበታል ያለው አምነስቲ፥ የባሉቺ ማህበረሰብ አባላት የሞት ቅጣቱ በስፋት የተፈጸመባቸው መሆናቸውን ገልጿል።
“የኢራን ባለስልጣናት ለሰው ልጅ ህይወት ምንም ክብር ሳያሳዩ በአደንዣዥ እጽ በተያያዘ ወንጀል የሞት ቅጣት ተፈጻሚ አድርገዋል” ያሉት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ጸሃፊ አንጌስ ካላማርድ፥
ሳኡዲ አረቢያ፣ ሶማሊያ እና አሜሪካም ኢራንን በመከተል ከፍተኛ የሞት ቅጣት የተመዘገበባቸው ሀገራት ናቸውብለዋል።
በአሜሪካ በ2023 24 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል፤ በተለያዩ ግዛቶች የተዋወቁ የሞት ቅጣት መፈጸሚያ መንገዶችም አሳሳቢ ናቸው ብለዋል ዋና ጸሃፊዋ።
በአላባማ የናይትሮጂን ጋዝን በመጠቅም የሞት ቅጣትን ለመፈጸም በጥር ወር አዲስ ህግ መጽደቁን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት አውስቷል።
ሪፖርቱ በ2023 የሞት ቅጣት የተፈጸመባቸው ሀገራት ቁጥር ወደ 16 ዝቅ ማለቱን መልካም ጅምር ነው ቢለውም እንደ አሜሪካ ባሉ ሀገራት የታየው አሃዝ ግን አሳሳቢ መሆኑን ጠቁሟል።
በ2022 የሞት ቅጣትን ተፈጻሚ አድርገው በነበሩት ቤላሩስ፣ ጃፓን፣ ማይናማር እና ደቡብ ሱዳን ባለፈው አመት በአንድም ሰው ላይ የሞት ቅጣት ተፈጻሚ አልሆነም ተብሏል።