በ2022፣ 883 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል - አምነስቲ ኢንተርናሽናል
ባለፈው አመት በ20 ሀገራት የተፈጸመው የሞት ቅጣት ከ2021 በ53 በመቶ ጭማሪ ያለው ነው ተብሏል
ኢራን፣ ሳኡዲ አረቢያ እና ግብጽ ከፍተኛውን የሞት ቅጣት የፈጸሙ ሀገራት መሆናቸው ተገልጿል
በ2022 የተፈጸመው የሞት ቅጣት ካለፉት አምስት አመታት ሁሉ ከፍተኛው መሆኑን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት አመላክቷል።
ድርጅሩ ባወጣው አመታዊ ሪፖርት በ2022 በሞት የተቀጡ ሰዎች ቁጥር 883 መሆኑን ገልጿል።
ይህም ከ2021 አመት ጋር ሲነጻጸር የ53 በመቶ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን ነው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያስታወቀው።
አሃዙ በ20 ሀገራት የተመዘገበ የሞት ቅጣትን የሚያመላክት ሲሆን፥ በርካታ ሰዎችን በሞት እንድምትቀጣ የሚነገርላትን ቻይና አላካተተም።
በሰሜን ኮሪያ፣ ቬትናም፣ ሶሪያ እና አፍጋኒስታንም የሞት ቅጣት መፈጸሙን ማረጋገጥ ቢቻልም በጥቂቱ ምን ያህል ሰዎች እርምጃ ተወስዶባቸዋል የሚለውን በትክክል ማረጋገጥ ባለመቻሉ በሪፖርቱ አልተካተተም ብሏል አምነስቲ ኢንተርናሽናል።
ኢራን፣ ሳኡዲ አረቢያ እና ግብጽ በ2022 ከተመዘገበው የሞት ቅጣት 90 በመቶውን ድርሻ ይይዛሉ።
በኢራን ብቻ 576 ሰዎች በሞት ተቀጥተዋል፤ ይህም በ2021 ከነበረው 314 ከፍተኛ ብልጫ ያለው ነው።
ቴህራን በሞት ከቀጣቻቸው ውስጥ 279ኙ በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ፣ 255ቱ ደግሞ ከአደንዛዥ እጽ ዝውውር ጋር በተያያዘ የተገደሉ ናቸው። በሀገር መክዳት ወንጀል የተከሰሱ (18) እንዲሁም የአስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈጸሙ (21) ሰዎችም በሞት ተቀጥተዋል።
የኢራንን ብሄራዊ ጥቅም አደጋ ላይ ጥለዋል ተብለው በሞት ከተቀጡት ውስጥ በህዳር ወር በተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ተሳትፎ የነበራቸው ይገኙበታል፤ የመንግስታቱ ድርጅትም ግድያውን ማውገዙ ይታወሳል።
በሳኡዲ አረቢያም በ2022 196 ሰዎች በሞት መቀጣታቸውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል አመታዊ ሪፖርት ያሳያል፤ ይህም ከ2021ዱ በሶስት እጥፍ ጭማሪ ያሳየና በ30 አመታት ውስጥ ከፍተኛው ነው ብሏል ሪፖርቱ።
ሪያድ 85 ሰዎችን በሽብርተኝነት፤ 57 ሰዎችን ደግሞ በአደንዛዥ እጽ ማዘዋወር ክስ በሞት ቀጥታለች።
በግብጽ በ2022 24 ሰዎች በሞት መቀጣታቸውን የሚያመላክተው ሪፖርቱ፥ አሃዙ ከ2021 የ71 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ስለመሆኑም ጠቅሷል።
በአሜሪካ (18)፣ ሲንጋፖር (11)፣ ኢራቅ (11)፣ ኩዌት (7)፣ ሶማሊያ(8)፣ ደቡብ ሱዳን (5) እና የመን (4) የሞት ቅጣት መመዝገቡንም የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት ጠቁሟል።
የድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አኜስ ካላማርድ የሞት ቅጣትን በስፋት የሚፈጽሙ በተለይ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት አለምአቀፍ ህጎችን ከመጣስ እንዲቆጠቡና ጫና ሊደረግባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።