ባለስልጣኑ ስምንት ዝሆኖች መገደላቸውን ሲያረጋግጥ፣የፓርኩ ዋርደን ደግሞ ከስድስቱ ዝሆኖች ጥርሳቸው መወሰዱን ገልጿል
ባለስልጣኑ ስምንት ዝሆኖች መገደላቸውን ሲያረጋግጥ፣የፓርኩ ዋርደን ደግሞ ከስድስቱ ዝሆኖች ጥርሳቸው መወሰዱን ገልጿል
በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በሚገኘው ማጎ ብሔራዊ ፓርክ ከሰሞኑ ዝሆኖች መገደላቸው ተሰምቷል፡፡ ከግንቦት 18 ቀን ጀምሮ ህገ-ወጥ አደን ላይ የተሰማሩ ሰዎች ባደረሱት ጥቃት በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ ዝሆኖች ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል፡፡ እስካሁን ስምንት ዝሆኖች መገደላቸው መረጋገጡን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አረጋግጧል፡፡
አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ዝሆን ሲገደል ከዚህ በፊት አጋጥሟቸው እንደማያውቅ የፓርኩ ዋርደን አቶ ጋናቡል ቡልሚ ለአል ዐይን አማርኛ አረጋግጠዋል፡፡
ከሶስት ቀን በፊት በማጎ ብሔራዊ ፓርኮ ውስጥ በህገ-ወጥ ታጣቂዎች በዝሆኖች ላይ በከፈቱት ተኩስ አምስት ዝሆኖች ቀድመው መሞታቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡
ጥቃቱ መቼ እና እንዴት ተፈጸመ?
የማጎ ብሔራዊ ፓርክ ዋርደን አቶ ጋናቡል ቡልሚ እንደገለጹት ጥቃቱ የተፈጸመው ግንቦት 18 ቀን 2012 ነው፡፡ “ከካሮ ከሃመር ማህበረሰብ የተውጣጡ ህገ-ወጥ አዳኞች” ዝሆኖቹ ውኃ ለመጠጣት እየሄዱ ሳለ ተኩስ ከፍተው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ጥቃት ካደረሱት ሕገ ወጥ አዳኞች መካከል ሁለቱ መጎዳታቸውን የገለጹት አቶ ጋናቡል ሌሎቹ ጥቃት አድራሾች ግን አለመያዛቸውን ነው ለአል ዐይን ያስታወቁት፡፡ እስካሁን ባለው መረጃም ስድስት ዝሆኖች መሞታቸውንና ጥርሳቸውም መወሰዱን የገለጹት ዋርደኑ ሌሎች ሁለት ዝሆኖች ግን መሞታቸውና አለመሞታቸው አለመረጋገጡን ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ሁለቱ ዝሆኖች በተከፈተው ተኩስ ሳይሞቱ እንዳልቀረ ገልጸዋል፡፡ከጥቃት አድራሾቹ አንዱ የቀድሞው የሃመር ወረዳ አፈጉባዔ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን ዝሆኖቹ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲሞክር ጉዳት ደርሶበት ሶዶ ሆሰፒታ ይገኛል ብለዋል፡፡በእንዲህ አይነት ሕገ ወጥ ስራዎች ላይ የሚሰማሩ አመራሮችም እንዳሉ ያነሱት አቶ ጋናቡል ብዙ ዝሆኖችን በአንድ ጊዜ የማጥቃት አበዜ ያልተለመደ ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡
አቶ ጋናቡል በዝሆኖች ላይ የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ በቅድሚያ ለሃመር ወረዳ አስተዳደር ማሳወቃቸውን ነው የተናገሩት፡፡
ጉዳዩን ለሃመር ወረዳ ካመለከቱ በኋላም የጸጥታ ሃይል፣የሃገር ሽማግሌ እና የወረዳ አመራሮች እንዲሄዱ ከደቡብ ኦሞ ዞን ትዕዛዝ እንደተላለፈም ተገልጿል፡፡ ይሁንና የጸጥታ ኃይል አያስፈልግም፣ በሀገር ሽማግሌዎች እና በወረዳ አመራሮች ብቻ ውይይት ይደረግ ተብሎ ለውይይት ጥሪ ሲደረግ አንወያይም የሚል ሃሳብ ከፓርኩ መነሳቱ ተገልጿል፡፡በዚህም ምክንያት ውይይት አለመደረጉን የፓርኩ ዋርደን አስታውቀዋል፡፡
በ2007ዓ.ም በተደረገ ቆጠራ በፓርኩ ውስጥ170 ዝሆኖች መመዝገባቸውን የገለጹት ዋርደኑ (የፓርኩ ጥበቃ) ዘንድሮ ሊቆጠር ዕቅድ ተይዞ ነበር ብለዋል፡፡ ነገር ግን ቆጠራው በኮሮና ምክንያት መቋረጡን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ እና የአረንጓዴ ሃሳቦች አቀንቃኝ አቶ ሰለሞን ወርቁ የደረሰው ጅምላ ጭፍጨፋ ለማስቆም እና ወንጀለኞችን ለማቅረብ የክልሉም ሆነ የዞን አመራሮች እስካሁን ድረስ ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዳቸውን ገልጸው ይህም ችግሩን የበለጠ የከፋ ሊያደርገው እንደሚችል አሳስበዋል፡
ቱሪዝም ጋዜጠኛው ሄኖክ ስዩም በበኩሉ በአፍሪካ አህጉር እንዲህ ያለ ወንጀል በአንድ ሰሞን የትም ሊደረግ እንደማይችል ገልጾ የደቡብ ክልል ስለወሰደው እርምጃና ስለተፈጸመው ወንጀል እስካሁን ምንም ያለው ነገር እንደሌለ እና እንደዚህ ያለ ወንጀልም በአሁኑ ብቻ ሳይሆን በሚመጣው ትውልድ ጭምር መፍረድ ስለመሆኑ ጽፏል፡፡ “የመጪውን ትውልድ ድርሻ መንጠቅ ነው” የሚለው ሄኖክ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስምምነት መፈረሟንና ለዝሆን ጥበቃ በሚል ከለጋሽ ሀገራት በርካታ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግላት አንስቷል፡፡
ዝሆን ለመጠበቅ በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ ፕሮጀክቶች አንደኛው እና ዋናው የማጎ ብሔራዊ ፓርክን ለትውልድ ለማሻገር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ያነሳው ጋዜጠኛው “የዓለምን ብር ቀርጥፈን እየበላን የራሳችንን ሀብት በማውደም ወደር የለሽ ሆነናል ፣ይህ በዓለም ፊት አንገታችንን የሚያስደፋ ኋላ ቀርነት ነው” ብሏል፡፡
የአረንጓዴ ሃሳቦች አመንጭና አቀንቃኝ ሰለሞን ወርቁ በበኩሉ የሚመለከተው ተቋም በአፋጣኝ ደርሶ ችግሩን መፍታት እንዳለበት ገልጾ ካልሆነ ግን የዝሆኖች ጭፍጨፋ እንቅስቃሴ ከዚህም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ሁሉም ሊገነዘብ እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ አቶ ሰለሞን አንድ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ስምንት ዝሆኖችን መግደል ትልቅ አደጋ መሆኑን አንስቷል፡፡
የማጎ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ክልል የሚገኝ የዝሆን መዳረሻ ሲሆን የዱር እንስሳቱ በከፍተኛ የጸጥታ ችግር ጉዳት ሲደርስባቸው የቆዩ መሆኑ ይገለጻል፡፡የፓርኩ ዋርደን አቶ ጋናቡል ቡልሚ እንደሚሉት አሁንም ይህንን ድርጊት የፈጸሙ አካላት የማያዳግም እርምጃ የማይወሰድባቸው ከሆነ ዝሆኑ የቀሩት ዝሆኖች ህይወት አደጋ ላይ መውደቁን አንስተዋል፡፡
የቱሪዝም ባለሙያዎቹ ሄኖክ ስዩም እና ባለሙያው ሰለሞን ወርቁ አሁን ላይ ይህንን ችግር ያደረሱት ሰዎች ላይ ከባድ እርምጃ እንዲወሰድ እየጠየቁ ናቸው፡፡ በፓርኩ የሚሰሩ ጠበቃዎችም ህይወታቸው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያሉት ዝሆኖች ከ1000 እንደማይበልጡ አቶ ሰለሞን ይገልጿሉ፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ግን የስምንት ዝሆኖች ህይወት ጠፍቷል፤ይህ ምናልባትም ለዝሆኖች አስከፊ ጊዜ መሆኑን ያመለክታል ሲሉም የሚገልጹ አሉ፡፡ በኢትዮጵያ የዝሆን መዳረሻ ሚባሉት ጋምቤላ፣ ኦሞ፣ ማጎ፣ቃፍታ ሽራሮ ፣ባቢሌ ፣ጨበራ ጩርጩራ መሆናቸው ይታወቃል፡፡