ታሪክ፣ሰንደቅ ዓላማና ሕገ መንግስት ምክክር ሊደረግባቸው ይችላሉ ከተባሉት ጉዳዮች መካከል ናቸው
በጦርነት፣ በድርቅ፣ በብሔር ግጭትና ንትርክ ላይ ባለችው ኢትዮጵያ፤ የዜጎች አብሮ የመኖር እሴትና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ መዳከሙን የፖለቲካና የማህበረሰብ አጥኝዎች ያነሳሉ፡፡
በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመምከር ያስችላል የተባለ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ ኮሚሽኑ የተቋቋመው፤ “በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች እንዲሁም የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ልዩነት እና አለመግባባት የሚታይ በመሆኑ፤ ይህንን ልዩነት እና አለመግባባት ለማርገብ እና ለመፍታት ሰፋፊ ሀገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ነው” ተብሏል፡፡
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከተቋቋመ በኋላ በርካቶች ምክክሩ የሀገሪቱን ቸግር ይፈታል ወይ? ጦርነቱ ሳያልቅ የሚደረገው ምክክር ነው ወይስ ድርድር? ምክከር የሚደረግባቸው ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እየተነሱ ነው፡፡
አል ዐይን አማርኛ ያነጋገራቸው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አለሙ አስፋው፤ ኮሚሽኑ እንደ መዋቅር ሀገራዊ በሆኑ መሰረታዊ ጉዳች ዙሪያ ለመመካከር የሚያስችል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ሁሉም ሰው አሸናፊ የሚሆንበትን ሁኔታ ለማምጣትም ኮሚሽኑ ጠቃሚ ሊሆን እንደሚችል አንስተዋል፡፡
አቶ አለሙ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረገው ቆይታ፣ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ መታደቁ ችግሮቹ ከውጊያ ወደ ጠረንጴዛ እንዲመጡ እንደሚያደርግም ገልጿል፡፡ በየጊዜው ክርክር የሚያስነሱ ጉዳዮች እንዳሉም ነው አቶ አለሙ የገለጹት፡፡ አቶ አለሙ በኢትዮጵያ ውስጥ ክርክር የሚነሳባቸው ጉዳዮች በርከት ቢሉም ታሪክ፣ ሰንደቅ ዓላማና ሕገ መንግስቱ ግን ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ መልካሙ ሹምዬም እንደ አቶ አለሙ ሁሉ ክርክር የሚነሳባቸውና በምክክሩ ውይይት ሊደረግባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አንስተዋል፡፡ በመሆኑም የሀገረ መንግሥቱ አወቃቀር (የክልሎች አወቃቀር)፣ የምርጫ ስርዓት፣የመንግሥት ሥርዓት፣ የፌደራል ሥርዓት (በክልሎችና ፌደራል መንግሥቱ መካከል፣ በክልሎች መካከል ስለሚኖር ግንኙነት)፣ የሕዝብ ቆጠራና ተያያዥ ጉዳዮች፣ የግልና ቡድን መብቶች ሚዛን እና የማኅበራዊ ውል መነሻና ምንጭ እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ የሽግግር ፍትሕ፣ የካሳና እርቅ ጉዳይ ምክክር ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን አቶ መልካሙ ያነሳሉ፡፡
አቶ መልካሙ ከዚህ ባለፈም ፤ የሕገ- መንግሥት ትርጉም ጉዳይ (ማን ይተርጉመው?)፣ የሰብአዊ መብቶችና መሰረታዊ ነጻነቶች፤ የፌደራል ፕሮጀክቶች ስርጭትና የኢኮኖሚ አሻጥር ጉዳይ፤ የሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እና መሰል የፖለቲካና ሕጋዊ ጉዳዮች (ሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች) ፤ ሰንደቅ ዓላማ እና ሌሎች ጉዳዮችም ምክክር ሊደረግባቸው ይገባል ይላሉ፡፡
አቶ አለሙ፤ ቢያንስ በየጊዜው “እኛን በሚያጣሉ ጉዳዮች ዙሪያ ንግግር ማድረጉ እንደሚበጅ ያነሱ ሲሆን፤ ምክክሩ በልሂቃን ብቻ የሚደረግ እንደማይሆን ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡ የተዘጋጀው ሰነድም ንግግሩ በልሂቃን መካከል ብቻ ይሆናል እንደማይል አቶ አለሙ አንስተዋል፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ መልካሙ ሹምዬ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በብዙ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ቅራኔዎች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ቅራኔዎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ በመሄዳቸው ምክክር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም በኢትዮጵያ ያሉት ቅራኔዎች ሀገር ወደ ማፍረስ ደረጃ እየደረሱ በመሆኑ እና እነዚህን በአግባቡ እየፈታ መሄድ የሚችል ሥርዓት ባለመኖሩ ሀገራዊ ምክክር መድረኩ መዘጋጀቱ ጠቃሚ እንደሚሆንም አቶ መልካሙ አንስተዋል፡፡
አቶ መልካሙ ሹምዬ ገለጻ በኢትዮጵያ ውስጥ በታሪክ ትርክት፣በሀገረምንግስት ግንባታ ሂደት እና በወደፊት ፍላገቶች ላይ ቅራኔዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
ያነጋገርናቸው ምሁራን እንደሚሉት ኮሚሽኑ ከሁሉም በፊት መሰረታዊ የሆኑ የፖለቲካ ወይም የሕገ-መንግሥት መርሆችን መለየት እንዳለበት አንስተዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም መሰረታዊ መርሆች መጠበቃቸውን የሚያረጋግጥ አካል ለአብነትም እንደ ሕገ- መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ዓይነት ተቋም ቢቋቋም የተሻለ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
አሁን ላይ የመንግስት ጦር በአማራ እና አፋር ድንበር አካባቢ ከህወሓት ኃይሎች ጋር ተፋጦ የሚገኝ ሲሆን መንግስት የህወሓት ኃይሎች ትንኮስ እያደረጉ መሆኑንና እርምጃም እየወሰደ መሆኑን ገልጿል፡፡
ህወሃት ግጭቱን በሰላም ለመፍታት ከመንግስት ጋር ሌላ አካል በኩል እየተነጋገረ መሆኑን ቢገልጽም፣መንግስት ክወሃት ጋር ድርድርም ሆነ ንግግር ጀምሯል መባሉ ሀሰት ነው ሲል አስተባብሏል፡፡
የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ ግጭቱን በሰላም ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ነው፤አሜሪካም በአፍሪካ ህብረት በኩል የሚደረገውን ጥሪት እንደምትደግፍ አስታውቃለች፡፡
በ2013 ዓ.ም ጥቅምት ወር በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲገደሉ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ እንዲፈናቀሉ ኑሯቸው እንዲመሰቃቀል ምክንያት ሆኗል፡፡