የዓለም ጤና ድርጅት 33.5 ሜትሪክ ቶን የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ትግራይ ክልል ማጓጓዝ ጀምሬያለሁ አለ
ዶ/ር ቴድሮስ ከወራት በፊት "በትግራይ በተጣለው ስልታዊ እገዳ ምክንያት የህክምና ቁሳቁስ መላክ አልተቻለም " ማለታቸው ይታወሳል
ዛሬ 10 ሜትሪክ ቶን የህክምና ቁሳቁስ ወደ ትግራይ ክልል መግባቱንም የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል
የዓለም ጤና ድርጅት 33 ነጥብ 5 ሜትሪክ ቶን የሚገመት አስፈላጊ የሆኑ መድሃኒቶችን እና የህክምና ቁሳቁሶችን ወደ ትግራይ ክልል ማጓጓዝ መጀመሩን አስታወቀ።
የድርጀቱ የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት በትዊተር ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ፤ “በቀን 10 ሜትሪክ ቶን የህክምና ቁሳቁስ ወደ ትግራይ ክልል ይገባል” ብሏል።
በዚሁ መሰረት በዛሬው እለት 10 ሜትሪክ ቶን የህክምና ቁሳቁሶችን በአውሮፕን ወደ ትግራይ ክልል መግቱን አስታውቋል።
የዓለም ጤና ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ የተመድ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ከፍተኛ የሆነ የህክምና ቁሳቁሶች እጥረት እንዳለ ሲገልጹ መቆየታቸው አይዘነጋም።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ባለፈው ህዳር ወር በሰጡት መግለጫ “መድሃኒት ወደ ትግራይ መላክ አንችልም ምክንያቱም እገዳ ተጥለዋል፤ እገዳው ስልታዊ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ/ኦቻ/ በትናትናው እለት ባወጣው ሪፖርት ፤ በመቀሌ ከተማ የሚገኘው የአይደር ሆስፒታል የነበሩትን የህክምና ቁሳቁሶች አሟጦ መጨረሱን ገልጾ ነበር
ከዚህ ቀደም ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ለተከታታይ አስር ቀናት የህክምና ቁሳቁሶችን በመጫን ወደ ትግራይ በረራዎች ማድረጉም ይታወቃል።
በረራዎቹ እንደ ኢንሱሊን፣ ሄሞዳያሊስስ፣ ኦክሲቶሲን፣ ቴታነስ ቶክሳይድ፣ ጓንት እና የቀዶ ጥገና ቁሳቁሶችን የመሳሰሉ አስፈላጊ መድሃኒቶችን እንደነበሩም ነው የዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በወቅቱ የገለጸው።
ኦቻ በበኩሉ ከየካቲት 2 እስከ 4/2022 በነበሩ ጊዜያት 14.5 ሜትሪክ ቶን የሚገመቱ እንደ አንቲባዮቲክስ፣ ግሉኮስ ለስኳር ህክምና፣ ፀረ-ትል፣ ፀረ-አለርጂ እና ፀረ- የፈንገስ መድኃኒቶች የመሳሰሉ መድሃኒቶች ወደ ትግራይ ክልል ማስገባቱ አስታውቋል፡፡
ይሁን እንጅ “በአየር ላይ የሚደረጉ የህይወት አድን ዕርዳታዎች ውስን እና በትግራይ ክልል ከሚያስፈልገው አንጻር ዝቅተኛ ናቸው” ሲል የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ/ኦቻ/ አሳስቧል።