“ባለፈው ስምንት ወር ያገኘነው የኤክስፖርት እድገት ባለፉት 20 ዓመታት ከነበረው ጋር አይነጻጸርም” ጠ/ሚ ዐቢይ
ኢትዮጵያ ተበድረው መክፈል ያልቻሉ ከሚባሉ ሀገራት ተርታ የተጠቀሰችው ከጂዲፒ አንጻርመሆኑን ገልጸዋል
ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የወጪ ንግዱ የ21 በመቶ እድገት ማሳየቱንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ በመስጠት ላይ ናቸው።
ከኑሮ ውድነት ፣ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፣ የብድር ጫና እና ተያያዥ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከምክር ቤቱ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግስታቸው ባለፉት 3 ዓመታት የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻይ ግቦችን ቀርጾ በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
የብድር ጫናን መቀነስ፣ የውጭ ንግድን ማሻሻል፣ የፕሮጀከቶችን አፈጻጸም ማሻሻል፣ ገቢን ማሻሻል፣ ገበያን ማረጋጋት፣ የእድገት ቀጣይነትን ማረጋገጥ የመንግስታቸው ዋነኛ ትኩረቶች እንደነበሩ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ያነሱት፡፡
ይሁንና ኮሮና ቫይረስ፣ ጎርፍ፣ አንበጣ እና በተለይ ደግሞ ግጭቶች እቅዱ በሚፈለገው ደረጃ ተፈጻሚነት እንዳይኖረው ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት 6.1 በመቶ ዓመታዊ እድገት ማስመዝገቧን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሔም በኮሮና ወቅት በዓለም የተመዘገበ ተምሳሌታዊ እድገት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህን ሁሉም ያምናሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ከዚህ በመነሳት ለዚህ ዓመትም ከኛ ጋር የቀረበ ትንበያ ይዘዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በዚህም እድገት “ለመጀመሪያ ጊዜ የነፍስ ወከፍ ገቢያችን 1 ሺህ ዶላር ደርሷል፤ ጥቅል ዓመታዊ ምርታችንም (ጂዲፒ) 100 ቢሊዮን ዶላር ተሻግሯል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ምንም እንኳን ከወቅታዊው ዓለማቀፋዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከውጭ የሚገባው የሬሚታንስ ገቢ ቢቀንስም ፣ የወጪ ንግድ ግን በመጨመር ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተቀዛቅዞ የነበረው “የወጪ ንግድ እያንሰራራ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የወጪ ንግዱ የ21 በመቶ እድገት አሳይቷል” ብለዋል። “ባለፈው ስምንት ወር ያገኘነው የኤክስፖርት እድገት ባለፉት 20 ዓመታት ከነበረው ጋር አይነጻጸርም” ያሉም ሲሆን በተለይ “የወርቅ ማዕድንኤክስፖርት በእጥፍ ማደግ ችሏል” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያለባትን የውጭ እዳ ጫና ባለፉት 3 ዓመታት ከነበረበት 37.6 በመቶ አሁን ላይ ወደ 26.8 በመቶ ዝቅ እንዲል ማድረግ እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡ በዚህም አገሪቱ የመበደር አቅሟ መስመር እንዲይዝ የማድረግ ቁመና ላይ እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ያለባት ብድር ከአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ያንሳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን ተበድረው መክፈል ያልቻሉ ከሚባሉ ሀገራት ተርታ ያደረሰን ከጂዲፒ አንጻር ነው፡፡
ገቢን ከማሳደግ አንጻርም ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ እድገት መመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። እነደ ጠቅላይ ሚኒስተሩ ገለጻ በ2010 ዓ.ም 176 ቢሊዮን ብር ገቢ ሲገኝ፣ በ2011 ዓ.ም 196.5 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም በ2012 ዓ.ም 228 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል። በዘንድሮው የ2013 ዓ.ም ያለፉት 8 ወራት ውስጥ ደግሞ 191 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ በሰጡት ምላሽ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት 6.1 በመቶ ዓመታዊ እድገት ማስመዝገቧን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሔም በኮሮና ወቅት በዓለም የተመዘገበ ተምሳሌታዊ እድገት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ይህን ሁሉም ያምናሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ከዚህ በመነሳት ለዚህ ዓመትም ከኛ ጋር የቀረበ ትንበያ ይዘዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡