ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የተላከ መልዕክትም ለሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አደረሱ
በጄኔራል ብርሃኑ ጁላ የተመራ የልኡካን ቡድን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝት እያደረገ ነው
ጄኔራል ብርሃኑ ለሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ ቀጣናው ወቅታዊ ሁኔታ አብራርተዋል
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከአቡዳቢ ልዑል አልጋ ወራሽ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ አዛዥ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር ዕሁድ የካቲት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተላከ መልዕክትም ለሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አድርሰዋል፡፡
በውይይታቸው ወቅት ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው ግንኙነት በሁሉም ዘርፍ እየተጠናከረ እንደመምጣቱ መጠን በሁለቱ ሀገራት የመከላከያ ተቋማት ያለው ግንኙነትም በዚያው ልክ እየተጠናከረ፣ የትብብር አድማሱም እየሰፋ መሄዱን ጠቅሰዋል፡፡
ልዑል ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ በበኩላቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተላከውን መልዕክት ከተቀበሉ በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ህዝቦቻቸውን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ እንዲሄድ ቁርጠኛ አቋም እንዳላትም ተናግረዋል።
የሀገራቱ ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በትምህርትና ቴክኖሎጂ፣ በደህንነትና ጸጥታ ዘርፍ፣ እንዲሁም በወታደራዊ ግንኙነቶች ይበልጥ እንዲጠናከር በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በኩል ያለውን ቁርጠኝነት በመጥቀስ የበኩላቸውም ጥረት እንደሚያደርጉም ነው የገለጹት፡፡
ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ከልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር በምስራቅ አፍሪካ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ፣ በትግራይ ክልል ስለተካሄደው የሕግ ማስከበር ወታደራዊ እርምጃ እንዲሁም አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታም አብራርተውላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በመጭዎቹ ቀናቶች ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የመከላከያ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጋር እንደሚመክሩም በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የባህር ኃይል አዛዥ ሪር አድሚራል ሜ/ጄኔራል ክንዱ ገዙ ከሪር አድሚራል ፓይለት ልዑል ሼክ ሰኢድ ቢን ሐምዳን ቢን መሀመድ አል ናህያን ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል፡፡