ፖለቲካ
የመከላከያ ሠራዊቱን እሴቶች የማይወክል ተግባር የሚፈጽሙትን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ
ዶ/ር ዐቢይ ከሰራዊቱ አመራሮች ጋር መምከራቸውን አስታውቀዋል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጠያቂነት እና የስነ ምግባር ክፍተቶች በተገቢው ስርዓት ርምጃ ይወሰድባቸዋል ብለዋል
የሃገር መከላከያ ሠራዊቱን እሴቶች የማይወክል ተግባር የሚፈጽሙትን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ጠዋት ከብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጋር መሰብሰባቸውን ገልጸዋል፡፡
“በስብሰባው ሠራዊታችን የሠላም ጠባቂ እና የሀገራችንን ሉዓላዊነት የሚያስከብር በመሆኑ የሚሰማኝን ኩራት ገልጫለሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠራዊቱን እሴቶች የማይወክል ተግባር የሚፈጽሙትን ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ አሳስቤያለሁ ብለዋል፡፡
“ስነ ምግባርን እና ሙያተኝነትን የማጠናከር እና በየትኛውም የሕግ ማስከበር ሥራ የመከላከያ ሠራዊታችንን እሴቶች የማይወክል ተግባር የሚፈጽሙትን ተጠያቂ ማድረግ፣ በአግባቡ ኃላፊነታቸውን የሚወጡትን መሸለም እንደሚገባ አሳስቤያለሁ”ም ነው ጠቅላይ ሚኒትሩ ያሉት።
“የተጠያቂነት እና የስነ ምግባር ክፍተቶች በተገቢው ስርዓት ርምጃ የሚወሰድባቸው” እንደሚሆንም በማህበራዊ ገጾቻቸው አስታውቀዋል።