በትግራይ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምክር ቤቱ ጸደቀ
የሚኒስትሮች ም/ቤት በትናትናው እለት ነው ለ6 ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጣው
መንግስት ትናንት በሰጠው መግለጫ ከሕወሓት ኃይል ጋር የሚደረገው ውጊያ እንደቀጠለ አስታውቋል
በትግራይ ክልል የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምክር ቤቱ ጸደቀ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመደበኛ ስብሰባው የሚኒስትሮች ምክር በትግራይ ክልል ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፀደቀ።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው እለት በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መሰብሰቢያ አደራሽ አካሂዷል።
የኢፌዴሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በትናትናው እለት ባደረገው 21ኛ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት ለ6 ወራት ተፈጻሚ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተውጣጡ አባላት ያሉት ግብረኃይል በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል።
ግብረኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን ‘‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሀይል’’ተብሎ
እንደሚጠራም ተገልጿል።
አዋጁ በመላው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ተፈፃሚ የሚደረግ ነው፡፡
ትናንት ምሽት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና መከላከያ ሰራዊት በሰጧቸው መግለጫዎች ከሕወሓት ኃይል ጋር የሚደረገው ውጊያ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ በትናንትናው የምሽት መግለጫቸው "በዛሬው ዕለት በነበረው ኦፐሬሽን በሁሉም ግንባር የጠላትን ፍላጎት ያኮላሸ ስራ ተሰርቷል" ብለዋል።
ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ተቀንሰው የነበሩ 3 መኮንኖች፡ ሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ ፣ ሌ/ጄኔራል ዮሐንስ ገ/መስቀል እና ሌ/ጄኔራል አበባው ታደሰ ሰራዊቱን ተቀላቅለው ስራ እንደጀመሩም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
መንግሥት ተገዶ ወደጦርነት ገብቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 4 ሰዓት ጀምሮ የነበረው የሕወሓት ትንኮሳ ሁሉ ከሽፏል ሲሉ ተናግረዋል። መከላከያ ሰራዊት ትንኮሳውን እስከመጨረሻው እንዲያከሽፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መከላከያ ሚኒስቴርም እንዲሁ ፣ሰራዊቱ በሰፈረባቸዉ ካምፖች የተከፈተበትን ጥቃት በብቃት መክቶ ወደ ጸረ ማጥቃት እርምጃ መሸጋገሩን አስታውቋል።