በተለያየ ቦታ ያለው ሰራዊት ወደ ጦርነቱ ቦታ እየተንቀሳቀሰ ነው- ጄነራል ብርሃኑ ጁላ
ኢሰመኮ “የጸጥታ ሀይሎች የሲቭል ሰዎችን ደህንነት” እንዲጠብቁ ጥሪ አቀረበ
ጄነራል ብርሃኑ “ሀገራችን ያላሰበችው ጦርነት ውስጥ ገብታለች፤ ይሄ ጦርነት አሳፋሪ ነው” ብለዋል
ጄነራል ብርሃኑ “ሀገራችን ያላሰበችው ጦርነት ውስጥ ገብታለች፤ ይሄ ጦርነት ጦርነት ነው” ብለዋል
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃነ ጁላ በብሄራዊ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ ከህወሓት ጋር ለሚደረገው ዉጊያ በተለያዩ የኢትጵዮጵያ ክፍል ያለው ሰራዊት ወደ ቦታው እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ሀገራችን ያላሰበችው ጦርነት ውስጥ ገብታለች፤ ይሄ ጦርነት አሳፋሪ ጦርነት ነው፡፡ አላማም የለውም፤ ሰራዊቱ ከውስጥ እወጋለሁ ብሎ አላሰበም ነበር” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከትናንት በስትያ ህወሓት በትግራይ ክልል በሚገኘው ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱንና፤ በህወሓት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸው ነበር፡፡
ጄነራል ብርሃኑ ህወሓት “ለእኩይ አላማ ያደረጀው ሃይል ሰራዊታችን ላይ ጥቃት አድርሷል፡፡ የትግራይ ህዝብ ይህንን አውዟል፤ ከመከላከያ ሰራዊታችንና ከመንግት ጋር መሆኑን አረጋግጧል ” ብለዋል፡፡
“በቀበሮ ጉዳድጓድ ውስጥ ሆኖ የትግራይን ህዝብና መንግስት በሚጠብቅ ሰራዊት”ላይ ነው ወረራ የደረሰበት ብለዋል፡፡
ሰራዊቱ ለተቃጣበት ጥቃት እጅ ባለመስጠት ጥቃቱን መመከት መቻሉን ጄነራል ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ ጄነራል ብርሃኑ ጦርነቱ ወደ መሀል ሀገር ሳይመጣ በዚያው እንደሚያልቅም ተናግረዋል፡፡
የትግራይ ክልል መንግስት በበኩሉ በድንበር አካባቢ ወታደራዊ እንቅስቃሴና የአየር በረራን ማገዱን አስታውቋል፤ ከፌደራል መንግስት የሚቃጣበትን ጥቃት መመከት በሚያስችለው ሁኔታ ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ የፌደራል እና የክልል የጸጥታ ሃይሎች የሰላማዊ ሰዎችን ደህንነት እንዲጠብቁና ሰብአዊ መብትን እንዳይጥሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል ያለው አለመግባባት የጀመረው ኢትዮጵያን ለ27 አመታት ሲመራ የነበረው ኢህአዴግ ፈርሶ ብልጽግና ፓርቲ ሲመሰረት ፣ ከመስራቾቹ አንዱ የነበረው ህወሓት የውህደቱ አካል አልሆንም ባለበት ወቅት ነበር፡፡
የፌደራል መንግስት በኢትዮጵያ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ምርጫ ለማካሄድ አያስችልም በማለት ምርጫ እንዲራዘም ሲያደርግ፣ ህወሓት በራሱ ክልልዊ ምርጫ አድርጎ ነበር፡፡
ህወሓት የፌደራል መንግስት ምርጫ ማካሄድ ሲገባው ከህገመንግስቱ ውጭ ነው ስልጣን ላይ ያለው ሲል ሲከስ ቆይቷል፡፡ መንግስትን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ የህወሓት ምርጫ ተቀባይነት እንደሌለው ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
የፌደራል መንግስት ከሳምንታት በፊት ከትግራይ ክልል ጋር ህጋዊ ግንኙነት ማቋረጡን አስታውቆ ነበር፡፡አሁን ላይ በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል የነበረው አለመግባባት ሁኔታው ተባብሶ ወደ ግጭት ሊያመራ ችሏል፡፡