“በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት ያወጁ የሩቅና የቅርብ ጠላቶችን ለመደምሰስ በሚያስችል ሙሉ ቁመና ላይ እንገኛለን”-ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል
በሰሜን ጎንደር ዞን ቀራቅር እና ሌሎች አካባቢዎች በቡድኑ ላይ በሰነዘረው ጥቃት ከፍተኛ ሰብዓዊና ማቴሪያላዊ ኪሳራ ማድረሱንም ነው ሰራዊቱ ያስታወቀው
“ሰራዊቱ በሰፈረባቸዉ ካምፖች የተከፈተበትን የከሃዲዎች ጥቃት በብቃት መክቶ ወደ ጸረ ማጥቃት እርምጃ ተሸጋግሯል”- መከላከያ ሠራዊት
“በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት ያወጁ የሩቅና የቅርብ ጠላቶችን ለመደምሰስ በሚያስችል ሙሉ ቁመና ላይ እንገኛለን”-ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል
ዛሬ በትግራይ ቴሌቪዥን በቀጥታ በተላለፈ መግለጫ ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ያብራሩት የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) “በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት ያወጁ የሩቅና የቅርብ ጠላቶችን ለመደምሰስ በሚያስችል ሙሉ ቁመና ላይ እንገኛለን”ሲሉ መናገራቸውን የቴሌቪዥን ጣቢያው ዘግቧል፡፡
ጣቢያው በማህበራዊ ገጹ በሰበር ባሰፈረው ዜና ርዕሰ መስተዳድሩ “የትግራይ የፀጥታ ኃይል የሰላም አማራጭ ረግጠው በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት ያወጁ የሩቅና የቅርብ ጠላቶችን ለመደምሰስ በሚያስችል ሙሉ ቁመና ላይ እንገኛለን” ብለዋል፡፡
“በትግራይ ክልል የነበረውን ጦር መሳርያ በመጠቀም ትግራይን ለመጨፍጨፍ የነበረው ህልም ሙሉ በሙሉ ከሽፏል፡፡ ለአቋማችን መስዋዕት ለመሆን ዝግጁ ነን፡፡ አሁን ከነሙሉ ወታደራዊ ትጥቃችን ተዘጋጅተናል፡፡ እነዚህ ጦር መሳርያዎች ትግራይን እንጠብቅባቸዋለን፡፡ ከየትኛውም አቅጣጫ ለሚቃጣብን ወረራ እንደመስስበታለን፡፡ አሁን ሙሉ በሙሉ ታጥቀናል” ሲሉም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የሚያስቀምጡት፡፡
በክልሉ የሚገኘው የሰሜን እዝ ሰራዊት ከትግራይ ህዝብ ጎን መሰለፉንም ነው የገለጹት፡፡
ይህ ተቃጥቶብናል ያሉትን ጦርነት በድል ለመወጣት እንደሚያስችላቸውም ተናግረዋል፡፡
ከ2 ዓመታት ከመንፈቅ በፊት ከመጣው ሃገራዊ ለውጥ ጋር በተያያዘ ከፌዴራል የስልጣን ቦታዎች የተገለለው የክልሉ መሪ ፓርቲ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አለኝ ባለው የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ምክንያት ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት ራሱን አግልሎ ቆይቷል፡፡
በኮሮና ወረርሽኝ በተራዘመው 6ኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ምክንያት የፌዴራሉ መንግስት ስልጣን መስከረም 30 እንደሚያበቃ እና ከዚያም በኋላ ህጋዊ ቅቡልነት ያለው የመንግስት አካል እንደማይኖር በማሳሰብ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጭምር ህገወጥ የተባለውን የራሱን ክልላዊ ምርጫ ማካሄዱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሚመራው የፌዴራል መንግስት ጋር አቃቅሮት ቆይቷል፡፡
ብሄርና ሃይማኖትን መነሻ አድርገው በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች በተለይም በተለያዩ የኦሮሚያ እና የቤንሻንጉል እንዲሁም የደቡብ ክልል አካባቢዎች ሲፈጸሙ በነበሩ ጥቃቶች የህወሓት እጅ እንዳለበት ሆኖ ሲገለጽ መሰንበቱ የሚታወስ ነው ምንም እንኳን ራሱን የፌዴራል መንግስቱን በህገ ወጥነት የሚፈርጀው ፓርቲው ቢያስተባብልም፡፡
ሁኔታዎች በውይይት እና በድርድር ከመፈታት ይልቅ እየተካረሩ መሄዳቸውን ተከትሎ ህወሓት የልዩ ኃይል እና የሚሊሻ አባላቱን ወደተለያዩ አዋሳኝ የክልሉ አካባቢዎች ሲያንቀሳቅስ ተስተውሏል፡፡
ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ማልደው ድንገተኛ ጋዜጣዊ መግለጫን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ህወሓት በክልሉ ሰፍሮ በሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት የጦር መሳሪያዎችን ለመዝረፍ ሙከራ ማድረጉን በመግለጽ ሰራዊቱ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዛቸውን አስታውቀዋል፡፡
“ሕወሐት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል። ይህ ሠራዊት ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት ነው። በቦታው የሚገኘውም የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው። ሕወሐት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ ሀገር ሠራዊት ቆጥሮ፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷል። በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል”ሲሉም ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ያሰፈሩት፡፡
“መንግሥት የትግራይ ሕዝብ እንዳይጎዳ በማሰብ፣ ጦርነት እንዳይፈጠር የትእግሥቱ ጫፍ ድረስ ታግሷል” ያሉት ዐቢይ አህመድ “ጦርነት የሚቀረው ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ባለመሆኑ” ወደዚያው መገባቱንም ነው የገለጹት፡፡
“የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል። ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። ሀገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ሆኗል”ም ብለዋል ህዝብ ከመከላከያው ጎን እንዲቆም ጥሪ ባደረጉበት መልዕክታቸው፡፡
መከላከያ ሠራዊቱም ከዚያን ወዲህ ተከፍቶብኛ ያለውን ድንገተኛ ጦርነት ለመግታት እና ለመደምሰስ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡
ትናንት በተሰጠ መግለጫም “ሰራዊቱ በሰፈረባቸዉ ካምፖች የተከፈተበትን የከሃዲዎች ጥቃት በብቃት መክቶ ወደ ጸረ ማጥቃት እርምጃ ተሸጋግሯል” መባሉ የሚታወስ ነው፡፡
ሰራዊቱ ከአማራ የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት በሰሜን ጎንደር ዞን ቀራቅር እና ሌሎች አካባቢዎች እብሪተኛ ባለው ቡድን ላይ በሰነዘረዉ ጥቃት ከፍተኛ ሰብዓዊና ማቴሪያላዊ ኪሳራ ማድረሱንም አስታውቋል፡፡
የቡድንና የነብስ ወከፍ መሳሪያዎችን መማረኩንም ጭምር ነው የገለጸው፡፡
በአማራ ክልል አዋሳኝ በሆኑት የሶሮቃ እና ቀራቅር አካባቢዎች በተደረገው ውጊያ በርካታ ያለፍላጎቱ እንዲዋጋ የተገደደ የፀጥታ ኃይል በሰላም እጁን መስጠቱን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ማስታወቃቸውም የዛሬ ዜና ነበረ፡፡
ለ6 ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጊዜ አዋጅ በክልሉ መታወጁ አይዘነጋም፡፡