በአፋር ክልል በተደረገ ህክምና አይናቸው የበራላቸው ታካሚዎች
የዐይን ሞራ ሕክምና በሱማሌ፣ በደቡብ፣ በአማራ እና በአፋር ተሰጥቷል
ህክምናው ከ98 በመቶ በላይ ውጤታማ መሆኑን የህክምናውን ቡድን የመሩት ዶ/ር ጌትነት ገልጸዋል
ወ/ሮ ሉባባ ሰኢድ በአፋር ክልል የዱብቲ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ በስራ ብዛት የተነሳ የግራ ዐይናቸው ማየት አይችልም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሰርተው ለመብላት ተቸግረው እንደነበር ያነሱት ወ/ሮ ሉባባ ከሰሞኑ የኩዌቱ ዳይሬክት ኤድ ባዘጋጀው የዐይን ሞራ ሕክምና የግራ ዐይናቸው ማየት ጀምሯል፡፡
``ዐይኔን አጥቼ ነበር አሁን አግኝቻለሁ`` የሚሉት ወ/ሮዋ አሁን ከአምስት ዓመት በኋላ የግራ ዐይናቸው ማየት መቻሉን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ህክምናው በዱብቲ ሆስፒታል ሲሰጥ የግራ ዐይናው በማየቱ የተደሰቱት ወ/ሮ ሉባባ “ምንም ሳልከፍል ዐይኔን ሰጥተውኛልና በጣም አመሰግናለሁ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሌላው በዱብቲ ሆስፒታል ዐይናቸውን ሲታከሙ ያገኘናቸው አቶ ሰኢድ አሕመድም በተመሳሳይ የግራ ዐይናቸው ማየት አይችልም ነበር፡፡ ዳይሬክት ኤድ ባዘጋጀው ዘመቻ የአቶ ሰኢድ ግራ ዐይን ማየት በመቻሉ ``ዐይኔን ድሮ ወደነበረው ተመልሶልኛል፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን አውጥታችሁናል” ብለዋል፡፡ አሁን ላይ ዐይናቸው ከማየቱም ባሻገር በልጅነታቸው እንደነበረው ማየት እንደቻለ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ዳይሬክት ኤድ ያዘጋጀውን የዐይን ሕክምና በበላይነት የሚመሩት ጠቅላላ ሀኪም እንዲሁም የዐይን ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ጌትነት ንጉሴ ከዚህ በፊት መሰል ሕክምናው በሱማሌ ፣ በደቡብ፣ በአማራ እና በአፋር መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
በአፋር ክልል ለሁለተኛ ጊዜ የዐይን ሞራ ሕክምና መደረጉን ያነሱት ዶ/ር ጌትነት ከዚህ በፊት በክልሉ 1ሺ 21 ሰዎች ሕክምናውን ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ቀደም ሲል በአፋር ክልል ህክምናውን ለ800 ሰዎች ለመስጠት ታቅዶ እንደነበር ያነሱ ሲሆን የተሰራው ግን ከዕቅድ በላይ ነበር ብለዋል፡፡ አሁንም በድጋሚ በዱብቲ ሆስፒታል በተሰጠው ህክምና 800 ሰዎች አገልግሎቱን አግኝተዋል፡፡ በዚህም መሰረት ስራው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን ገልጸው ረጅም ጊዜ ማየት ያልቻሉ እያዩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ጌትነት “ትልቁ ጉልበታችን ዛሬ ተሰርቶ ነገ ማየት መቻላቸው ነው” ያሉ ሲሆን 13 ዓመትና ከዛ በላይ ሳያዩ የቆዩት ሰዎች ማየት ሲችሉ በጣም ደስተኛ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ማታ ህክምናው ተሰጥቶ ጠዋት ማየት ሲችሉ ደስታን እንደሚፈጥር የገለጹት ዶ/ር ጌትነት፤ የዐይን ሞራ ሕክምና 98 በመቶ እና ከዛ በላይ ውጤታማ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ 1 ሚሊዮን 800 ሺ ዜጎች ዐይነ ስውር ሲሆኑ ከዚህ ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነው የዐይን ሞራ ግርዶሽ ነው ተብሏል፡፡ ከ 700 ሺ እስከ 800 ሺ የሚሆኑት ሰዎች በሞራ ምክንያት ዐይነ ስወር እንደሆኑም ዶ/ር ጌትነት ገልጸዋል፡፡
የዱብቲ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶ/ር መሐመድ የሱፍ ፤ አፋር ክልል በረሃማ ስለሆነ የዐይን ሞራ ግርዶሽ እንደሚበዛበት ገልጸው ይህንን ችግርም ከዳይሬክት ኤድ ጋር በመተባበር እንዲሰራ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ኃላፊው ከዚህ በፊት ከ 150 እስከ 200 የሚሆኑ ሰዎችን ማከም ቢቻልም አሁን ግን ብዙ ሰዎች ህክምናውን እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሕክምናውን ካገኙት መካከል አንዲት እናት ሁለቱም ዐይናቸውን በማጣታቸው ምክንያት አዲስ የተወለደች የልጅ ልጃቸው ሳያዩ ከቆዩ ከዓመታት በኋላ ማየት መቻላቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡
በዚህ ህክምና ምክንያትም ሴትዮዋ በድምጽ ብቻ የሚያውቋትን የልጅ ልቻውን ማየት እንደቻሉ የቢሮ ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡
የኩዌት ግብረ ሰናይ ድርጅት ዳይሬክት ኤድ የኢትዮጵያ ኃላፊ ጠሃ ማህሙድ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳሉት ፣ ከዚህ በፊት በአፋር ክልል ዱብቲ ሆስፒታል ለ800 ሰዎች የዓይነ ቀዶ ጥገና አገልግሎት ለመስጠት ታቅዶ 1 ሺ 21 ቀዶ ህክምና በሁለት ሳምንት ውስጥ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ሕክምናው በሱማሌ ክልል፣ በደቡብ፣ በአማራ እና በአፋር መሰጠቱን የገለጹት ኃላፊው በአማራ ክልልም በዚህ ሰሞን እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የዓይን የቀዶ ህክምና አገልግሎት መስጠት የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2009 ዓ.ም በሱማሌ ክልል ጐዴ ከተማ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
አቶ ጠሃ ህክምናው በአራት ካምፖች ማለትም ሁለት በአፋር ክልል እና ሁለት በአማራ ክልል ደሴ ከተማ በአጠቃላይ 3600 ሰዎች ህክምናውን አግኝተዋል፡፡
እስካሁን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ 22 ሺ 542 የዐይን ቀዶ ጥገና አገልግሎት መሰጠቱንም አቶ ታሃ ተናግረዋል፡፡
የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ያሲን ሀቢብ ዳይሬክት ኤድ በክልሉ ላደረገው አስተዋጽኦ የኩዌት ሕዝብና መንግስትን አመስግነው፤ ከዐይን ህክምና በተጨማሪም ድጋፍና ዕርዳታ ለሚፈልገው ለአፋር ሕዝብ ሌሎች ጉዳዮችንም እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡