ህወሓት “በወልቃይትና ራያ” በኩል “እዋጋለሁ ካለ የከፋ እርምጃ” እንደሚወሰድበት መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ
አሁን ላይ “ሕወሃት ስጋት አይደለም“ ብሏል ሰራዊቱ
የኢትዮጵያ መንግስት “ህወሃት አሁንም ኤርትራ ወደ ጦርነት እንድትገባ እየጋበዘ ነው“ ብሏል
ኤርትራ ጦሯን ብታስወጣም ህወሃት ግን ኤርትራን “ተከትዬ እወጋለሁ እያለ“ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ከሰሞኑ የታወጀው የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት እና ወታደሮችን ከመቀሌ የማስወጣቱ ሂደት በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ጋዜጣዊ መግለጫ ፤ ሕወሓት ኤርትራ ተመልሳ ወደ ጦርነት እንድትገባ እየጋበዘ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ፤ ሕወሓት የሽምቅ ውጊያውን ከኢትዮጵያ ሰራዊት ጋር ከመዋጋት ይልቅ ሕዝቡን ከፊት አድርጎ ሲዋጋ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
”ህወሃት መከላከያውን በዘር ነበር ያደራጁት፡፡ አሁንም በዘር ሲቀሰቅሱ የመጀመሪያቸው አይደለም” ያሉት ሌተናል ጀኔራል ባጫ፤ የሕዝብ ንብረት እንደተወሰደ በማስመሰል ሕዝቡን ለማሳመን አሊያም ”ሕዝቡን እየገደሉ በማስፈራራት ውጊያው ከህዝቡ ጋር እንዲሆን ቀይረዋል፤ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በተለይም ተምቤን ላይ ሕዝቡ ከመከላከያ ጋር እንዲጋጭ አድርገዋል” ብለዋል፡፡
ቀደም ሲልም ሕብረተሰቡን በማነሳሳት አስገድዶ በመድፈር፤ ለዘር ቅስቀሳ ማነሳሻ እንዳደረጋቸውም ነው የተገለጸው፡፡ የህወሃት ታጣቂዎች፤ የመከለከያን የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) ለብሰው ሴቶችን መድፈራቸውንና ከዛም በኋላ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ማሳበባቸውን የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ አንስተዋል፡፡
ዋና አስተባባሪው “የኛ ዓላማ የህዝቡን ህይወት መጠበቅ እንጂ መሳሪያ አለኝ ብሎ መረሸን አይደለም፤ የነበረውን የሽምቅ ውጊያ አካሔድ ወደዚህ ቀይረዋል” ፡፡ በመንግስት የሚፈለጉት ጄኔራሎች ከ10 ፤ ሲቪሎቹ ደግሞ ከ8 የማይበልጡ መሆኑን ያነሱ ሲሆን ፤ ወደ 50ሺ ሰራዊት ትግራይ ገብቶ እንደነበር አንስተዋል፡፡
መንግስት ትግራይን ለቆ ለመውጣት የወሰነው፤ ዓላማው የሕግ የበላይነትን ማስከበር እንጂ መቀሌን መያዝ አለመሆኑን ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ ጠቅሰዋል፡፡
መቀሌ ከዚህ በፊት የነበራት ወታደራዊ ዋጋ እና አሁን ያለው ሁኔታ እንደሚለያይ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ያኔ ስጋት እንደነበረ ገልጸው፤ እዛ የተሰማራው የወንጀል ኃይል እና እስረኞች “ከኛ ወታደር በላይ ነው” ብለዋል፡፡
“ለኛ አሁን ላይ መቀሌ ያንን ያህል ኃይል ማስቀመጥ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም“ ያሉት ዋና አስተባባሪው ህወሃት አሁን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት አለመሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ህወሃት ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም እንደሚጓዝ መግለጹን ተከትሎ” አሸባሪ አይታወቅምና “ህወሃት ወደ ወልቃይትና ራያ እንዳይመጣ ሰራዊቱ በተጠንቀቅ ቆሟል“ ተብሏል፡፡
የሰራዊቱ ከትግራይ ክልል መውጣት ጠቃሚ እንደሆነ የገለጹት ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ ሰራዊቱ አሁን ወጣ እንጅ ለመውጣት ከታሰበ መቆቱን ገልጸዋል፡፡ ሕወሃት አሁን ላይ ስጋት እንዳልሆነም ተገልጿል፡፡
“ህወሃት ትንኮሳ ካደረገ ምላሹ የእጥፍ እጥፍ ነው የሚሆነው” ያሉት ሌተናል ጀኔራል ባጫ፤ ቡድኑ መጀመሪያ ያቀደው፤ በአማራ እና በአፋር ክልል አድርጎ አዲስ አበባ መግባት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ ይህ ስጋት ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል ነው ያሉት፡፡ አሁን ላይ ህወሃት ይጠናከል የሚለው የሚያሳስብ ነገር እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን ይሁንና የኢትዮጵያ ሰራዊት ለሁሉም ነገር ዝግጁ መሆኑ ተልጿል፡፡
መንግስት ህወሃት እንዳይጠናከር ብቻ አይደለም እንዳይኖርም እንደሚሰራ ያነሱት የሥራ ኃላፊው ትንኮሳ ከመጣ “የገቡበት እንገባለን፤ ወደውጭ ሚወጡበት ምንም በር የለም” ብለዋል ሌተናል ጀኔራል ባጫ፡፡
ህወሃት ከዚህ በኋላ መሳሪያ ሊያገኝ የሚችልበት ምንም መንገድ እንደሌለና ሁሉም መንገዶች መዘጋታቸውን ሌተናል ጀኔራል ባጫ ተናግረዋል፡፡
ሮይተርስ የህወሓት ቃል አቃባይ የሆነውን ጌታቸው ረዳን ጠቅሶ እንደዘገበው ህወሓት የትግራይ ዋና ከተማ መቀሌን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩንና ሁሉም አካባቢ ከጠላት ነጻ እስከሚሆን ድረስ ወደ ደቡብ ወደ ምስራቅ እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል፡፡
ቃል አቀባዩ እንዳሉት አስፈላጊ ከሆነ ኤርትራና አማራ ክልል ድረስ በመግባት ጠላት ያሏቸውን እንደሚዋጉ መናገራቸውን ዘግቧል፡፡
መንግስት ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበለትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ባለፈው ሰኞ እለት ነበር ያስታወቀው፡፡ የመንግስትን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ተመድ፣አሜሪካና የአፍሪካ ህብረት በአዎንታ እንደሚያዩት ገልጸዋል፡፡