የህወሓት ኃይሎች ላሊበላን ከተቆጣጠሩ በኋላ በት/ቤቶች ካምፕ ሰርተው መቀመጣቸውን ነዋሪዎች ገለጹ
በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አፋርና አማራ ክልል የተስፋፋው ግጭት 10 ወራት ሊሆነው ነው
በአማራና አፋር ክልል በተስፋፋው ግጭት ምክንያት 220ሺ ሰዎች መፈናቀላቸውን መንግስት አስታውቋል
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካች ምክር ቤት አሸባሪ በሚል የፈረጀው የህወሃት ሀይሎች በአማራ ክልል ስር የምትገኘውን ታሪካዊቷን የላሊበላ ከተማ መቆጣጠራቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የህወሓት ሀይሎች ላሊበላ ከተማን ዛሬ ቀን አካባቢ ከተቆጣጠሩ በኋላ በከተማዋ በሚገኙ 3 ት/ቤቶች ካምፖችን ስርተው መቀመጣቸውን የከተማዋ ነዋሪ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ በከተማ ምንም አይነት የተኩስ ድምጽ አለመኖሩንም ተግረዋል፡፡
ያነጋገርናቸው ነዋሪ በስጋት ምክንያት ወጣቶች ከተማውን ለቀው መሸሻቸውን ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው የነበረው የጸጥታ ሃይል ቀደም ብሎ ከተማውን ለቆ መውጣቱን የገጹት ነዋሪ የህወሓት ሃይሎች ሲገቡም ምንም አይነት ተኩም ሆነ ጦርነት አልነበረም ብለዋል፡፡
ከሌሊት ጀምሮ ነዋሪው፣ ፖሊስ የጸጥታ ኃይሎች ጭምር ከተማውን ለቀው መውጣታቸውንና የባንክ እና ሌሎች የአገልግሎት ተቋማት መዘጋታቸውን አንድ የባንክ ባለሙያ የሆኑ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
“ምንም ላደርግ የምችለው አማራጭ ባለመኖሩ እኔም ከሌሎች ባልደረቦቼ ጋር በመሆን ከተማውን ለቅቄ ወጣሁ” የሚሉት ባለሙያው ሌሎች የሙያ ባልደረቦቻቸው ይህንኑ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡
“ረጅም የእግር ጉዞ በማድረግ ደህንነታቸው በሚጠበቅበት ስፍራ ማረፋቸውንም ገልጸልናል፡፡”
ከ8 ወራት ግጭት በኋላ የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ ከትግራይ ክልል ሰራዊቱን ማስወጣቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት ወደ አጎራባች አማራ አፋር ክልሎች ሊስፋፋ ችሏል፡፡
በተስፋፋው ግጭት ምክንያት በአማራና አፋር ክልሎች 220ሺ ሰዎች መፈናቀላቸውን መንግስት ሰሞኑን አስታውቋል፡፡ የህወሓት ሃይሎች ከላሊበላ ቀደም ብሎ አላማጣና ኮረምና መቆጣጠራቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡
የፌደራል መንግስት ጥቅምት 24፣2013ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሱን ካሳወቁ በኋላ በትግራይ ክልል “የህግ ማስከበር ዘመቻ” በመጀመሩ ግጭቱ መከሰቱ ይታወቃል፡፡
በትግራይ ክልል በነበረው ግጭት የሰብአዊ መብት ጥሰት መከሰቱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ አለምአቀፍ የመብት ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ መንግስትም በትግራይ ክልል በሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ በተሳተፉ ላይ እርምጃ እንደሚወስድና የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ ምርመራ ማካሄድ የሚፈልጉ ተቋማት ማካሄድ እንደሚችሉ መግለጹ ይታወሳል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ህወሓት ወረራ ፈጽሞብኛል በማለት ወረራውን ለመከላከል የክተት አዋጅ ማወጁ ይታወሳል፡፡ ከአማራ ክልል በተጨማሪ በርካታ ክልሎች ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን ህወሓትን ለመዋጋት የጸጥታ ሀይሎቻቸውን ማሰማራታቸውም ይታወሳል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አለምአቀፍ ተቋማቶች የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስና ግጭቱ በውይይተ እንዲፈታ ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡