በአፋር ክልል ህወሓት በፈጸመው ጥቃት 107 ህጻናትን ጨምሮ 240 ተፋናቃዮች መግደሉን የክልሉ መንግስት አስታወቀ
የክልሉ መንግስት ከያሎና ጎሊና ወረዳዎች ተፈናቅለው ጋሊኮማ ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት በተጠለሉ አርብቶ አደሮች ላይ ነው ጥቃት የተፈጸመው ብሏል
በጥቃቱ በመጋዘን ውስጥ የነበረ ከ30 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተፈናቃዮች የቀረበ አስቸኳይ የምግብና አልባሳት እርዳታ ወድሟል
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካች ምክር ቤት አሸባሪ በሚል የፈረጀው ህወሃት በአፋር ክልል በፈጸመው ጥቃት 107 ህጻናትን ጨምሮ የ240 ተፋናቃዮች መግደሉን የክልሉ መንግስት አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ ህወሃት ከያሎና ጎሊና ወረዳዎች ተፈናቅለው ጋሊኮማ ጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤት ተጠልለው በነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮች ላይ “አሰቃቂ ጭፍጨፋ” ማካሄዱን አስታውቋል።
“ህወሃት ተጠልለው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ አርብቶ አደር ማህበረሰብ ላይ በከባድ መሳሪያ (በመድፍ፣ በሞርታር እንዲሁም በታንክ) የታገዘ ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት እጅግ ዘግናኝ የሆነ ዘር የማጥፋት ጭፍጨፋ ፈፅሟል” ብሏል።
በጥቃቱም በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የነበሩ 107 ህጻናት፣ 89 ሴቶች እና 44 አዛውንቶች በድምሩ የ240 ሰዎች መሞታቸውን የመጀመሪያ ሪፖርት እንደደረሰው የክልሉ መንግስት የኮሙዩኒኬሽን አስታውቋል።
በተጨማሪም ህወሃት ለተፈናቃዮች በጋሊኮማ የሚገኘውን የምግብ መጋዘን በከባድ መሳሪያ ማጋየቱንም ነው የክልሉ መንግስት ያስታወቀው።
በጥቃቱ መጋዘኑ ውስጥ የነበረ ከ30, ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተፈናቃዮች የቀረበ አስቸኳይ የምግብና አልባሳት እርዳታ ሙሉ በሙሉ መውደሙን አስታውቋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግስት ሀገረመንግስቱን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር ላይ ተሳትፏል ያለውን ህወሓትን በሽብርተኝነት መፈረጁ ይታወሳል።
በትግራይ ክልል በፌደራል መንግስትና ትግራይን ክልል ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ግጭት ከተጀመረ ከ8 ወር በኋላ የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፣መከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ ማስወጣቱ ይታወሳል።
የፌደራል መንግስት ሰራዊቱን ከትግራይ ያስወጣው የትግራይን ቀውስ በውይይት ለመፍታት በማቀዱ መሆኑን ቢገልጽም ግጭቱ አሁን ላይ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፏፍቷል።
ጥቅምት 24፣2013 በትግራይ ክልል የተጀመረው ግጭት አሁን ላይ ወደ አማራና አፋር ክልሎችም የተስፋፋ ተስፋፍቷል፡፡ መከላከያ ሰራዊትና የሁለቱ ክልሎች የጸጥታ አካላት የህወሓትን እንቅስቃሴ ለመግታት ጥቃት መክፈታቸውም መንግስት አስታውቋል።