አሜሪካ ህወሓት ሕፃናትን ለወታደርነት “እየመለመለ ነው”መባሉ እንዳሳሰባት ገለጸች
በትግራይ ክልል የተጀመረው ግጭት ወደ አፋርና አማራ ክልል ተስፏፍቷል
አሜሪካና ዩኔስኮ ህወሓት የዓለም ቅርስ የሆኑትን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን እንዲጠብቅ አሳስበዋል
አሜሪካ ህወሓት ሕፃናትን ወታደር እንዲሆኑ “እየመለመለ ነው”የሚለው ሪፖርት እንዳሳሰበው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ አስታወቁ፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በሰጡት መግለጫ በቡድኑ ውስጥ ሕጻናት ወታደር ሆነው መሰለፋቸውን እንደሰሙ የገለጹት ቃል አቀባዩ ይህም ሀገራቸውን እንደሚያሳስባት ተናግረዋል፡፡
አሜሪካ፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ህወሓት የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገቡትን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እንዲጠብቅ አሳስባለች፡፡
አሜሪካ ይህን ያለችው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ የፈረጀው ህወሃት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የምትገኘውን የላሊበላ ከተማ አስተዳደርን መቆጣጠሩን ተከትሎ ነው፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ላሊበላን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ቃል አቀባዩ በምላሻቸው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምስክር እና የመካከለኛው ዘመን ስልጣኔ መገኛ በመሆኑ ሊጠበቅ እንደሚገባ ተናረዋል፡፡ ላሊበላ የኢትዮጵያን ልዩ መሆን፤ ብዝኃነትን፤ በባህል ቅርስ የበለጸገች መሆኗን እንዲሁም ሁሉንም የሀገሪቱን ዜጎች አንድ የሚያደርግ ቅርስ መሆኑንም አሜሪካ ገልጻለች፡፡
ኔድ ፕራይስ የህወሃት ሃይሎች ላሊበላ ከተማ መግባታቸውን መስማታቸውን አስታውቀው፤ቡድኑ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እንዲጠበቁ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ የህወሃት ቡድን ቅርሱ ጉዳት እንዳይደርስበት ሊጠብቅ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ የህወሃት ቡድን ከአማራ እና አፋር ክልሎች እንዲወጣም አሜሪካ ጠይቃለች፡፡
በላሊበላ ከተማ በአንድ የግል ባንክ ይሰራ የነበረ ነዋሪ በትናንትናው እለት ለአል ዐይን እንደገለጸው የህወሓት ቡድን በገነተ ማሪያም አድርጎ ወደ ላሊበላ መግባቱን እና እርሱን ጨምሮ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ገጠር ቀበሌዎች መሸሻቸውን ተናግሯል፡፡
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው የትግራይ ተወላጆች፤በጸጥታ ኃይሎች እየታሰሩ እና እየተንገላቱ መሆኑን መስማታቸው ገልጸው ጉዳዩ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል፡፡
በፌደራል መንግስትና ትግራይን ክልል ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ግጭት ከተጀመረ ከ8 ወር በኋላ የፌደራል መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፣መከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡ የፌደራል መንግስት ሰራዊቱን ከትግራይ ያስወጣው የትግራይን ቀውስ በውይይት ለመፍታት በማቀዱ መሆኑን ቢገልጽም ግጭቱ አሁን ላይ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ተስፏፍቷል፡፡ የአማራና የአፋር ክልሎችም ህወሓት ወረራ እንደፈጸመባቸውና ይህን እንደሚከላሉም ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡