ዶ/ር ኦንጋይ ኦዳን የደቡብ ክልል የኢዜማ የመሪ ክንፍ ተጠሪ ሆነው እንዲሰሩም ወስኗል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በመንግስት የተሾሙ አመራርና አባላቱ በተረከቡት ስልጣን ይቀጥሉ ሲል ወሰነ።
ፓርቲው በፌስቡከ ገጹ ባወጣው መግለጫ ወሳኔው በአርባ ምንጭ ከተማ ለሁለት ቀናት ተሰብስበው በነበሩት የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እና የፓርቲው ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) እና ሌሎችም የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች የተሰጠ ነው።
ከስብሰባቸው ጎን ለጎን ከፌደራል እስከ ወረዳ ባሉ የመንግስት መዋቅሮች ተካተው ሕዝብን በማገልገል ላይ ከሚገኙ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ጋር በሥራ አፈጻጸም እና በአደረጃጀት ጉዳዮች ላይ የተወያዩት ከፍተኛ አመራሮቹ ጉዳዩን የተመለከተ ውሳኔ አሳልፈዋል።
በውሳኔው መሰረትም መንግስት አብሮ ለመሥራት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በመዋቅሩ ተካተው ሥልጣን ተረክበው ሕዝብን በማገልገል ላይ የሚገኙ የኢዜማ አባላት አርአያ መሆን የሚችሉ ስለሆኑ በኃላፊነታቸው እንዲጥሉ መደረጉን መግለጫው ጠቅሷል፡፡
በመልካም ሥነምግባር የታነጹ፣ ሌብነትን የሚጸየፉ፣ በሥራ ትጋታቸው እና በአፈጻጸም ብቃታቸው የተመሠከረላቸው እና አርአያ መሆናቸውን እንዲቀጥሉም ማሳሰብያ ተሰጥቷል እንደ ፓርቲው ገለጻ።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በስብሰባቸው በደቡብ ክልል በመንግስት መዋቅር ውስጥ ስለተካተቱ አባላት አደረጃጀት እና ተጠሪነት የመከሩም ሲሆን ኦንጋይ ኦዳ (ዶ/ር) በደቡብ ክልል የኢዜማ የመሪ ክንፍ ተጠሪ ሆነው እንዲሰሩ መወሰናቸው ተገልጿል፡፡
ኢዜማ በመጀመርያ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤው ከመንግስት የቀረበውን የአብረን እንስራ ጥሪ ተቀብሎ መንግስት ለከፍተኛ አመራሮቹ ጭምር የሰጠውን ሹመት መቀበሉ ይታወሳል።
በዚህም የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በፌዴራል መንግስት ካቢኔ ውስጥ ተካተው በትምህርት ሚኒስትርነት ሲሾሙ፤ የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ካቢኔ ተካተው የአስተዳደሩ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሆነው ተሾመው በማገልገል ላይ ናቸው።
በደቡብ ክልል የመንግስት መዋቅር ውስጥ የተካተቱ የድርጅቱ አባላትም አሉ።
ሆኖም ይህ ኢዜማ የበለጠ እንዲዳከምና "የመንግስት ተለጣፊ" ሆኖ እንዲታይ አድርጎታል የሚሉ ወቀሳዎች ከራሱ ከፓርቲው ሰዎች ጭምር እንዲሰነዘሩ ምክንያት ሆኗል።
ጉዳዩ፤ የፓርቲው አቋምና አካሄድ ጭምር በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀር የልዩነት ምንጭ ሆኖ ፓርቲውን አመራር ለመቀየር እስከሚያስችል ምርጫ እስከማካሄድ አድርሶት እንደነበር ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የፓርቲው አንደኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ሰኔ 26 ቀን 2014 ዓ.ም ባደረገው ምርጫ ፕ/ር ብርሀኑ ነጋን እና አርክቴክት ዮሐንስ መኮንንን መሪ እና ምክትል መሪ አድርጎ መምረጡ የሚታወስ ነው፡፡