ለአዲስ አበባ ከንቲባነት የተወዳደሩት ክቡር ገና ከኢዜማ አባልነት ለቀቁ
አቶ ክቡር፤ “ኢዜማ ከገዢው ፓርቲ ጋር በመለጠፍ መስመሩን መሳቱ እጅግ የሚያሳዝነኝ ጉዳይ ነው ብለዋል”
ከአባልነት ለቀቁት ከፖለቲካዊ አቋምና "ህሊናን ካለመሸጥ" ውስጣዊ ውሳኔ ጭምር የመጣ እንደሆነ ተናግረዋል
ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባነት የተወዳደሩት አቶ ክቡር ገና ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መልቀቃቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ገለጹ።
አቶ ክቡር ደብዳቤው የተጻፈው መጋቢት ላይ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ አሁን የየትኛውም ፓርቲ አባል አለመሆናቸውን ተናግረዋል ።
ደብዳቤው ለፓርቲው ስለመድረሱ የጠየቅናቸው አቶ ክቡር አሁንም ደብዳቤው የወጣው ከፓርቲው መሆንለአል ዐይን ገልጸዋል።
አቶ ክቡር የመልቀቂያ ደብዳቤውን ለፓርቲው ሊቀመንበር በመጻፋቸው ፤ አል ዐይንም ከሊቀመንበሩ የሺዋስ አሰፋ ቆይታ አድርጎ ነበር።
አቶ ሺዋስ እስኪ ደብዳቤውን ልየው የሚል ሀሳብ ብቻ ሰጥተዋል።
አቶ ክቡር ከአባልነት ለመልቀቅ የወሰኑት ከግለሰባዊ አቋምና አመለካከት የመነጨ ብቻ ሳይሆን፣ ከፖለቲካዊ አቋምና "ህሊናን ካለመሸጥ" ውስጣዊ ውሳኔ ጭምር የመጣ እንደሆነ ተናግረዋል።
ግለሰቡ የፓርቲው አባል ሆነው በቆዩባቸው ጊዜያት የተወሰነ ቅሬታ የፈጠጠሩባቸውና ያሳዘኗቸው ጉዳዮች እንዳሉ ተናግረዋል።
አቶ ክቡር ከፓርቲው አባልነት ለመልቀቅ የወሰኑት ከተጨባጭ እውነታ ጋር ላለመጋፈጥ፣ በተለይ ደግሞ ፓርቲውን እያጋጠሙት ካሉት ወቅታዊ ፈተናዎች ለማምለጥ እንዳልሆነም ጠቅሰዋል።
ከዚህ ይልቅ አቶ ክቡር ኢዜማ ብልጽግና ፓርቲን በአደባባይ በይፋ እንዳይተችና እንዳይገዳደር ፈቅዶ የገባበት ተገቢ ያልሆነ የሁለቱ ፓርቲዎች ስምምነት ወይም አጋርነት ያስከተለው ተገቢ ውሳኔ እንደሆነ ሊታወቅልኝ ይገባል ብለዋል፡፡
ኢዜማ እንደ አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ለህዝብ የገባውን ቃል እና የተቋቋመበትን ዋነኛ አላማ እና ግብ ከማሳካት ይልቅ፣ ከገዢው ፓርቲ ጋር በመለጠፍ መስመሩን መሳቱ እጅግ የሚያሳዝነኝ ጉዳይ ነው ሲሉም አቶ ክቡር ተናግረዋል፡፡
በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ መድረኮች ፓርቲው ከተነሳበት አላማ ባፈነገጠ መልኩ ለገዢው ፓርቲ ያሳየው መለሳለስ ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ፣ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ እንደ ፓርቲ አመራርም እንደ አባልም የቻሉትን ሁሉ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበርም ገልጸዋል።
ኢዜማ ለምን በምርጫው ተሸነፍኩ ብሎ ራሱን ከመጠየቅና ስህተቶቹን በማረም፣ ድክመቶቹን በማከምና ራሱን የበለጠ በማጠናከር ዘመኑን በዋጀ አካሄድ ለአዲስ የፖለቲካ ትግል ከመነሳት ይልቅ የገዢው ፓርቲ ተለጣፊ ሆኖ መቀጠልን መርጧል ሲሉም ነው አቶ ክቡር የተናገሩት፡፡
ገዢው ፓርቲ የሚያቀነቅነው የብሔር ፌዴራሊዝም የሚያስከትላቸውን "አውዳሚ" ውጤቶች መደገፍና አላማና ግብን ለ"ሽርፍራፊ ስልጣን መስዋዕት አቅርቦ ከብሔር ፖለቲካ መዋቅር ጎን መሰለፍ፣ ለኢዜማ ለራሱም ሆነ ለአገሪቱ ፖለቲካ ብሎም ለነገዋ ኢትዮጵያ የሚበጅ በጎ አካሄድ ነው ብዬ አላምንም" የሚል ሃሳብም ተሰጥተዋል ፡፡
አቶ ክቡር ይህንን የመልቀቂያ ደብዳቤ የጻፉት ለፓርቲው ሊቀ መንበር የሺዋስ አሰፋ ነው።