ኢዜማ፤ መንግስት የመጨረሻ አቅሙን ተጠቅሞ ለዜጎች ጥበቃ ሊያደርግ ይገባል ሲል አሳሰበ
ፓርቲው ከደኅንነት ስጋቶች ለመውጣት የተቀናጀ ስልታዊ አቅጣጫ ይቀመጥ ሲልም አሳስቧል
በአማራ ክልል ሁለት አጎራባች ዞኖች አካባቢ ያጋጠሙትን የጸጥታ ችግሮች የተመለከቱ መረጃዎች እንደደረሱት አስታውቋል
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መንግስት የመጨረሻ አቅሙን ተጠቅሞ ለዜጎች ጥበቃ ሊያደርግ ይገባል ሲል አሳሰበ፡፡
መንግስት የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን እንዲያደርግ ሲያሳስብ መቆየቱን ያስታወሰው ኢዜማ ችግሮች ከተከሰቱም በኋላ በቶሎ መፍትሔ በመስጠት ከተቻለ አደጋዎቹን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ፤ ካልሆነም ጉዳቱን ለመቀነስ የመጨረሻ የሚባለውን አቅሙን ተጠቅሞ ጥበቃ ሊያደርግ ይገባል ሲል አሁንም አሳስቧል፡፡
ከትላንት እሁድ ሃምሌ 3 ቀን 2014 ዓ/ም ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አጎራባች አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች ማጋጠማቸውን የተመለከቱ መረጃዎች በአካባቢው ከሚገኙ አባላቱ እንደደረሱት አስታውቋል፡፡
በመሆኑም "መንግስት በተደጋጋሚ የገለፅነውን ማሳሰብያ የጸጥታ ችግር በተደጋጋሚ በሚከሰትባቸው አካባቢዎች ላይ አትኩሮት በመስጠት እና በመተግበር ዜጎች ላይ ከሚደርስ የህይወት እና የንብረት ጉዳት እንዲጠብቅ እንዲሁም ስጋቱ ወደሌላ አከባቢዎች እንዳይዛመት የማድረግ ሀላፊነቱን እንዲወጣ" እንጠይቃለን ነው ኢዜማ በይፋዊ የማህበረሰብ ትስስር ገጹ ያለው።
"በዚህ እጅግ ውስብስብ የደኅንነት ስጋት በብዙ የሀገራችን ክፍሎች ባለበት ወቅት ለህይወታቸው ሳይሳሱ ሀገር እየጠበቁ ያሉ የፀጥታ አካላት ከባድ መስዋዕትነት እየከፈሉም ተፈላጊው ውጤት ሳይመጣ እንዳይቀር የፖለቲካው አመራር ግዴታውን በአግባቡ ተገንዝቦ ተገቢውን አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ" ሲልም ጠይቋል።
ቀደም ሲል የተጠቀሰውን አካባቢ ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በአጠቃላይ ካሉት የደኅንነት ስጋቶች ለመውጣት የተቀናጀ ስልታዊ አቅጣጫ እንዲቀመጥ ሲልም ነው ኢዜማ ያሳሰበው።
በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ በጤ ቀበሌን እና በኤፍራታና ግድም ወረዳ አርሶ አምባ (ዘምቦ) ቀበሌን በሚያጎራብቱ አጎራባች አካባቢዎች (ጎጦች) ያጋጠመውን ግጭት ለማርገብ የክልሉና የፌዴራል የጸጥታ አካላት ወደ አካባቢው ማቅናታቸውን አል ዐይን አማርኛ መዘገቡ ይታወሳል፡፡