ኪሊያን ምባፔ ወደ ሪያል ማድሪድ ሊዛወር እንደሚችል እየተነገረ ነው
ፈረንሳዊው አጥቂ ኪሊያን ምባፔ የሳኡዲው ክለብ አል ሂላል ያቀረበለትን የዝውውር ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ተነገረ።
የአል ሂላል ልኡካን ፓሪስ ድረስ ቢያቀኑም ሊያነጋግራቸው አልፈቀደም ተብሏል።
ከፒኤስጂ ጋር ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ወደ ጃፓን ያቀናው የ24 አመቱ ተጫዋች አራት ጊዜ የእስያ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ካነሳው አል ሂላል የቀረበለትን አጓጊ ኮንትራት ስላለመቀበሉ በይፋ አልተናገረም።
ከወደ ፓሪስ የሚወጡ ዘገባዎች ግን የሳኡዲው ክለብ ተወካዮች የዝውውር ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን እየጠቆሙ ነው።
አል ሂላል ለተጨዋቹ እስከ 700 ሚልዮን ዩሮ የሚያስገኝ የአንድ አመት ውል እንዲሁም ለፒኤስጂ 300 ሚሊዮን ዩሮ የዝውውር ሒሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ፒኤስጂም ምባፔ ከአል ሂላል ጋር መደራደር እንደሚችል ፈቅዶለት እንደነበር አይዘነጋም።
ተጫዋቹ ከሳኡዲው ክለብ የቀረበለትን ክብረወሰን የሆነ የዝውውር ጥያቄ ያልተቀበለው ወደ ስፔኑ ክለብ ሪያል ማድሪድ ለመዛወር ጫፍ ላይ ስለደረሰ ነው የሚሉ ዘገባዎችም እየወጡ ነው።
አል ሂላል ሩበን ኔቬስን ከወልቭስ፤ ካሊዱ ኩሉባሊን ከቼልሲ እንዲሁም ሰርጌ ሚሊንኮቪችን ከላዚዮ ማስፈረሙ ይታወሳል።