ሳዲዮ ማኔ የሳኡዲ አረቢያውን አል ናስርን ሊቀላቀል ይችላል የሚል ሪፖርት ወጣ
የቀድሞ የሊቨርፑሉ ኮከብ ማኔ አል ናስርን የሚቀላቀል ከሆነ በክለቡ ከሮናልዶ ጋር ይጣመራል
ባየር ሙኒክ እንዳስታወቀው ሴኔጋላዊው አጥቂ ሳዲዮ ማኔ "ስለክለብ መቀየር" እየተነጋገረ ነበር
ሳዲዮ ማኔ የሳኡዲውን አል ናስር ክለብ ሊቀላቀል እንደሚችል እየተነገረ ነው።
ማኔ ፖርቹጋላዊ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶ የተቀላቀለበት አል ናስር ክለብ መዳረሻው እንደሚሆን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ፍራንስ24 ዘግቧል።
ከጃፖኑ የወዳጅነት ጨዋታ ውጭ ያደረገው የጀርመን ክለቦች አሸናፊ የሆነው ባየር ሙኒክ በፌስቡክ ገጹ"ሳዲዮ ማኔ ክለብ ለመቀየር በመነጋገር ላይ ስለሆነ በዛሬው ጨዋታ አይሰለፍም" ብሏል።
የ31 አመቱ የቀድሞ የሊቨርፑል ኮከብ ሀብታሞቹን የሳኡዲ ክለቦች የሚቀላቀል ከሆነ ከሮናልዶ እና ቤንዜማ ቀጥሎ ትልቅ ስም ያለው ተጨዋች እንደሚሆን ይጠበቃል።
የባይር ሙኒክ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል ስለጉዳይ በግልጽ ከመናገር ተቆጥበዋል።
"አሁን በዝውውር መስኮት ውስጥ ነን፤ ምን እንደሚካሄድ እና ነገሮች ምን እንደሚሆኑ ማየትን አመርጣለሁ" ሲሉ በወዳጅነት ጨዋታ የጃፖኑን ክዋሳኪ ፍሮንታልን 1 ለ 0 ካሸነፉ በኋላ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ማኔ ለአል ናስር የሚፈርም ከሆነ የአምስት ጊዜ ባሎንዶር አሸናፊ ከሆነው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ጋር ይጣመራል።
ማኔ በስድስት የውድድር ዘመኖች ከሞሀመድ ሳላህ እና ፍርሚኖ ጋር በመጣመር ለሊቨርፑል ኘሪሚየር ሊግ እና ሻምፒዮንስ ሊግ ማሸነፍ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
በባየር ሙኒክ ጥሩ ጅምር አሳይቶ የነበረው ማኔ በቦንደስ ሊጋ ጨዋታ ከወርደር ብርሜን በነበረው ጨዋታ ያጋጠመው ጉዳት በኳታሩ የአለም ዋንጫ ለሀገሩ እንዳይጫወት አስገድዶታል።
ማኔ በውድድር ዘመኑ በተሳተፈባየው 38 ጨዋታዎች 12 ጎሎች አስቆጥሯል፤ ይህ ከተጠበቀው በታች ሆኗል።
ሴኔጋላዊው አጥቂ በባየርሙኒክ የሁለት አመት የኮንትራት ጊዜ እየቀረው ነው ክለቡ ሊለቀው ነው የሚሉ ሪፖርቶች እየወጡ የሚገኙት።
ማኔ ሀገሩ ሲኔጋል በፈረንጆቹ 2022 የተካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ እንድታነሳ የጎላ አስተዋጽኦ ማድረጉ የሚታወስ ነው።