ፌስቡክ የ20 አመት ጉዞ፤ ከዶርም እስከ 3 ቢሊየን ተጠቃሚ
ማርክ ዙከርበርግና ጓደኞቹ በሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ያስተዋወቁት “ዘፌስቡክ” ትናንት 20ኛ አመት ልደቱን አክብሯል
ኢንተርኔት ከሚጠቀም የአለም ህዝብ ግማሹ የሚጎበኘው ፌስቡክ፥ በወር ከ3 ቢሊየን በላይ ተጠቃሚ አለው
የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ተማሪው ማርክ ዙከርበርግ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የሰራው የማህበራዊ ትስስር ገጽ ፌስቡክ ትናንት 20 አመት ደፍኗል።
ዙከርበርግ ከፌስቡክ በፊት ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ሴቶች ውቧ የትኛዋ ናት የሚልና ተማሪዎች አስተያየት የሚሰጡበት “ፌስማሽ” የተሰኘ ድረገጽ አስተዋውቆ ነበር።
የ19 አመቱ ዙከርበርግ የዩኒቨርሲቲውን የመረጃ ስርአት ሰብሮ የሴት ተማሪዎችን ፎቶ ከመታወቂያቸው ላይ በመውሰድ የሰራው ድረገጽ ወዲያውኑ በመዘጋቱም “ዘፌስቡክ”ተወለደ።
የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች በኢሜል አድራሻቸው የሚገቡበትና ከጓደኞቻቸው ጋር መልዕክት የሚለዋወጡበት፣ አዳዲስ ጓደኞች የሚያገኙበት “ዘፌስቡክ” በፈረንጆቹ የካቲት 4 2004 ተዋውቋል።
ዙከርበርግና ጓደኞቹ ለሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሰሩት ፌስቡክ አለም ሲያዳርስ ግን ጊዜ አልፈጀበትም።
በአሁኑ ወቅት በወር ከ3 ቢሊየን በላይ ተጠቃሚ ያለው ፌስቡክ፥ ተቀባይነቱ እያደገ እንዲሄድ በየጊዜው ማሻሻያዎችን ማድረጉ ይታወቃል።
በሁለት አስርት አመት ጉዞውም ከካምብሪጅ አናሊይቲካ ቅሌት እስከ ምርጫ ጣልቃገብነት በመረጃ አያያዙ በርካታ ክሶች ሲቀርቡበት ቆይተዋል።
የፌስቡክ ጅማሮ እና እድገት ምን እንደሚመስል በዝርዝር እንመልከት፦
2004
ዙከርበርግና ጓደኞቹ በየካቲት 4 2004 “ዘፌስቡክ” የተሰኘ ማህበራዊ ትስስር ገጽን ሲፈጥሩ ከሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ውጭ ተጠቃሚ አልነበረውም።
”ዘፌስቡክ” መልዕክት መለዋወጥ፣ መረጃ መለጠፍ እና በሌሎች ልጥፍ ላይ አስተያየት መስጠት ብቻ ነበር የሚያስችለው።
ይሄው አዲስ የትስስር ገጽ ከተዋወቀ ከቀናት በኋላ ሶስት የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዙከርበርግ “ኮኔክትዩ” የተሰኘ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ሃሳባችን ነው ወደ “ዘፌስቡክ” የወሰደው በሚል ከሰውታል። ክሱ ዙከርበርግ በ2008 ለከሳሾቹ የ65 ሚሊየን ዶላር በመክፈል መዘጋቱ የሚታወስ ነው።
2005
በፌስቡክ ላይ ፎቶዎችን መለጠፍ የተጀመረው፤ የራስን መለያ ፎቶ (ፕሮፋይል) ጥቅም ላይ የዋለው ከ2005 ጀምሮ ነው። Facebook.com የሚለውን ዶሜን አባውትፌስ ከተሰኘ ኩባንያ በመግዛት ከ”ዘፌስቡክ” ወደ “ፌስቡክ” የተሸጋገረውም በዚህ አመት ነው።
2006
ፌስቡክ የመጀመሪያው የአይፎን ስማርት ስልክ ከመለቀቁ ከአንድ አመት በፊት ለስማርት ስልኮች የሚሆን መተግበሪያውን አስተዋውቋል። በዚሁ አመትም ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባሻገር ማንኛውም የኢሜል አድራሻ ያለውና ከ18 አመት በላይ እድሜ ያለው ሰው የፌስቡክ አካውንት እንዲከፍት ፈቅዷል።
2007
ፌስቡክ በተመሰረተ አራተኛ አመቱ ቪዲዮው መጫንን ጨምሮ፣ ማስታወቂያዎችን መለጠፍና ማስተዋወቅ የሚያስችሉ ገጾችን መክፈት የሚያስችሉ አሰራሮችን አስተዋውቋል። የግል ኩባንያዎች እና የመንግስት ተቋማት ከግለሰብ የፌስቡክ አድራሻዎች የተለዩ የራሳቸው ገጾችን መክፈት የጀመሩት በ2007 ነው።
2008
ፌስቡክ መልዕክት መለዋወጥ የሚያስችለውን “ቻት” ሳጥን ያስተዋወቀው በ2008 ነው። ይህም በ2011 ራሱን ችሎ “ሜሴንጀር” የተሰኘ የመልዕክት መለዋወጫ መሆን ችሏል። የፌስቡክ የመረጃ ስርአት ተሰብሮ ከ80 ሚሊየን በላይ የማህበራዊ ትስስር ገጹ ተጠቃሚዎች የትውልድ ቀን የተለቀቀውም በዚሁ አመት ነበር።
2009
ፌስቡክ የ”ላይክ” ቁልፍን ያስተዋወቀው፣ ፎቶዎችን ለጓደኞቻችን ታግ ማድረግ እንዲሁም አስተያየት መስጫ ሳጥኑን የከፈተው በ2009 ነበር።
2010
ፌስቡክ በ2010 አጋማሽ ከ500 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎችን በማፍራቱ በአሜሪካ ኦሪገን ግዙፍ የመረጃ ማዕከል ከፍቷል። በተለያየ ሙያ፣ ማህበር እና የስራ ዘርፍ ያሉ ሰዎች የሚሰባሰቡበት “ግሩፕ” መክፈት የተጀመረውም በዚሁ አመት ነበር።
2011
ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን የጓደኞች ዝርዝር ያለፈቃዳቸው እንዲታይ በማድረግ የግል መብታቸውን ተዳፍሯል በሚል በአሜሪካ የንግድ ኮሚሽን ክስ ቀርቦበታል።
2012
በሚያዚያ ወር 2012 ዙከርበርግ የፎቶ ማጋሪያውን ኢንስታግራም በ1 ቢሊየን ዶላር ገዝቷል። በዚሁ አመት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 1 ቢሊየን (ከሰባት ሰዎች አንዱ ይጠቀመዋል) በመድረስም አዲስ ታሪክ አጽፏል።
2013
በሰኔ ወር 2013 የ6 ሚሊየን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ኢሜል አድራሻ እና ስልክ ቁጥር ተጠልፎ ኦንላይን ተለቋል። ተጠቃሚዎች የለጠፉትን (ፖስት) አርትኦት መስራት፣ ኢሞጂ እና ስቲከሮችን መጠቀም የተጀመረውም በ2013 እንደነበር ይታወሳል።
2014
ዙከርበርግ ኢንስታግራምን ከገዛ ከሁለት አመት በኋላ ዋትስአፕን ገዝቷል። በአሁኑ ወቅት ኢንተርኔት ከሚጠቀመው የአለም ህዝብ ግማሹ ዋትስአፕ ተጠቃሚ ነው።
2015
የብሪታንያው አማካሪ ድርጅት ካምብሪጅ አናሊይቲካ የሚሊየኖች የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መረጃ ያለፈቃዳቸው በመውሰድ ለፖለቲካዊ ማስታወቂያዎች ጥቅም ላይ አውሎታል የሚለው ክስ በዘጋርዲያን እና ኒውዮርክ ታይምስ ይፋ የተደረገው በ2015 ነበር።
ኩባንያው ብሪታንያ ከአውሮፓ ህብረት ለመነጠል ባደረገችው የህዝበ ውሳኔ የመራጮችን አቋም የሚያዛቡ መረጃዎችን ሲያሰራጭ ነበር የሚል ወቀሳ ቀርቦበታል።
“የካምብሪጅ አናሊይቲካ ቅሌት” ፌስቡክ ከአሜሪካ ፖለቲከኞች ጫና እንዲበዛበት ያደረገ ሲሆን፥ የኩባንያውን ዝና እና ገቢ በእጅጉ ጎድቶታል።
2016
ፌስቡክ በቀጥታ ቪዲዮዎችን ማሰራጨት የጀመረው በ2016 ነው።
2017
ለ24 ስአት የሚቆዩ ምስሎች (ስቶሪስ) በኢንስታግራም ከተዋወቁ ከአንድ አመት በኋላ ፌስቡክ ጥቅም ላይ ያዋላቸው በ2017 ነው። 360 ዲግሪ በማዘዋወር ልንመለከታቸው የምንችላቸውን ምስሎች (ፓናሮሚክ) መለጠፍ የተጀመረውም በዚሁ አመት ነው።
2018
የካምብሪጅ ኣአናሊቲካ ቅሌት ዳግም ሚዲያዎች ተቆጣጥሮ የለንደን የፌስቡክ ቢሮ ጥቃት ደርሶበት ዙከርበርግም በአሜሪካ ኮንግረንስ ቀርቦ ለመጀመሪያ ጊዜ ማብራሪያ የሰጠበት አመት ነው።
የመረጃ መንታፊዎች የ50 ሚሊየን የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን አካውንት ሰብረው የገቡትም በ2018 ነበር።
2019
ፌስቡክ በ2019 ሶስት ግዙፍ የመረጃ ስርቆት ገጥሞታል። ከ540 ሚሊየን በላይ የማህበራዊ ትስስር ገጹ ተጠቃሚዎች መረጃ ለህዝብ ይፋ ተደርጎ የፌስቡክ ተአማኒነት በእጅጉ ጥያቄ ውስጥ ወድቆ ነበር። የመረጃ ስርቆቱ ፌስቡክ ከ5 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ መድቦ የመረጃ ስርአቱን አስተማማኝ ለማድረግ ቃል እንዲገባ አስገድዷል።
2020
ፌስቡክ የተጠቃሚዎቹን የግል ነጻነት ባለማክበሩ የተላለፈበት የ5 ቢሊየን ዶላር ቅጣት ከፍሏል።
2021
ፌስቡክ በስሩ ያሉትን እንደ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ ያሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾችን በስሩ አድርጎ ሜታ ተሰኝቷል።
2022
የ14 አመቷ እንግሊዛዊ ሞሊ ሩሴል በመኝታ ክፍሏ ሞታ መገኘቷ ከፌስቡክ ጋር ተያይዟል።
በኢንስታግራም እና ፒንትረስት ላይ ራስን ስለማጥፋት መረጃዎች መጋራታቸው ለሞት ዳርጓታል በሚልም በፌስቡክ ላይ ክስ መመስረቱ ይታወሳል።
2023
ፌስቡክ ከ21 ሺህ በላይ ሰራተኞቹን ለማሰናበት ማቀዱን ያሳወቀበት አመት ነው። ትዊተርን ለመግዛት ከኤለን መስክ ጋር ተፎካክሮ ያልተሳካለት ሜታ “ትሪድስ” የተሰኘ ትዊተርን መሳይ መተግበሪያ አስተዋውቋል።
2024
በመረጃ አያያዝ እና ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ይዘቶች ቁጥጥር ላይ ክስ የበዛበት ሜታ መስራች ማርክ ዙከርበርግ ፍርድቤት ቀርቦ ይቅርታ ጠይቋል።
በየካቲት 4 2004 የተዋወቀው ፌስቡክ ክሶች ቢበዙበትም አሁን ላይ ወርሃዊ ተጠቃሚዎቹ 3 ቢሊየን ደርሰዋል።
በዶርም ውስጥ የተፈጠረው የማህበራዊ ትስስር ገጽ አሁን 1 ትሪሊየን ዶላር የሚገመት ሀብት ሆኖ ማርክ ዙከርበርግን የአለማችን አራተኛው ባለጸጋ አድርጎታል