የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ ራሳቸውን ከዓለም ፍጻሜ ለመጠበቅ በሚል መጠለያ እየገነቡ መሆኑ ተገለጸ
ባለጸጋው በሀዋይ ደሴት ውስጥ ባለ መሬት ውስጥ በ100 ሚሊዮን ዶላር መጠለያ በመገንባት ላይ ናቸው
ይህ የክፉ ቀን መጠለያ ቦታ የአደጋ ጊዜ መውጫን ጨምሮ ቅንጡ መገልገያዎችን ያሟላ ነው ተብሏል
የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ ራሳቸውን ከዓለም ፍጻሜ ለመጠበቅ በሚል መጠለያ እየገነቡ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ፌስቡክን ጨምሮ አራት የዓለማችን ታዋቂ የትስስር ገጾችን በባለቤትነት የያዙት አሜሪካዊው ማርክ ዙከርበርክ ለዓለም ፍጻሜ እየተዘጋጁ መሆኑ ተገልጿል፡፡
120 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሀብት ያላቸው ዙከርበርግ በሀዋይ ደሴት ውስጥ በክፉ ቀን የሚጠለሉበት ስፍራ በመገንባት ላይ መሆናቸውን ኒዮርክ ፖስት ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ዙከርበርግ የደሴቲቱን ስፍራ በ170 ሚሊዮን ዶላር ከዓመታት በፊት የገዙት ሲሆን አሁን ደግሞ በዚህ ስፍራ ላይ ቅንጡ የክፉ ጊዜ መኖሪያ ቤት እየገነቡ ነው፡፡
ይህ ስፍራ ለኑሮ አስፈላጊ የሚባሉ ምግቦችን ማምረት፣ የኤሌክትሪክ ሀይል፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረጊያ ሜዳ፣ ውሃ ዋና እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን ሙሉ ለሙሉ ከዚሁ ስፍራ ማግኘት በሚያስችል መልኩ በመገንባት ላይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ከ10 በላይ ቅንጡ ህንጻዎች እየተገነቡ እንደሆነ በተገለጸው ይህ የክፉ ጊዜ መጠለያ 30 መኝታ ቤቶች፣ 30 መታጠቢያ ቤቶች ህንጻዎቹ እርስ በርስ መገናኘት የሚያስችሉ ተገጣጣሚ ድልድዮች አላቸውም ተብሏል፡፡
ይህ የክፉ ጊዜ መጠለያ ስፍራዎች ፍንዳታዎች እና ሌሎች አደጋዎችን መቆጣጠር እና መከላከል በሚያስችሉ መንገድ በመገንባት ላይ እንደሆኑ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ይህ መጠለያ ቤተ መጽሃፍትንም ያካተተ ሲሆን በሁሉም ስፍራዎች 24 ሰዓት የሚያገለግሉ እጅግ ዘመናዊ ካሜራ፣ ማንኛውንም ደምጽ ማስገባት እና ማስወጣት በማይቻልበት ሁኔታ እየተገነቡም ነው ተብሏል፡፡
የፌስቡክ እለታዊ ተጠቃሚ ቁጥር 2 ቢሊየን ደረሰ
የፌስቡክ ኩባንያ ቃል አቀባይ እንዳሉት በሀዋይ ደሴት ውስጥ እየተገነባ ያለው የክፉ ጊዜ መጠለያ ስፍራ ማርክ ዙከርበርግ እና ቤተሰባቸው የሚጠለሉበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በዚህ የክፉ ጊዜ መጠለያ ህንጻው ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች ምንም ነገር ከውጪ አይገባም የተባለ ሲሆን የሚጠጣ ውሃ እና ምግብ የሚመረትበት 1 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶለታል፡፡
ዘገባውን ተከትሎም ማርክ ዙከርበርግ ምን ሰምተው ይሆን ይህን ያህል እየተዘጋጁ ያሉት? የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ቢሆንም ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል ተብሏል፡፡