ሜታ ኩባንያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 34 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ተገለጸ
ድርጅቱ 89 ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ገቢ የማግኘት እቅድ እንደነበረው አስታውቋል
አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እና የሰራተኛ ቅነሳ ማድረጉ ለኩባንያው ትርፍ መጨመር ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው ተብሏል
ሜታ ኩባንያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 34 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ተገለጸ።
በማርክ ዙከርበርግ የሚመራው ሜታ ኩባንያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የትርፍ ማሽቆልቆል አጋጥሞት ቆይቷል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሜታን ጨምሮ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከፍተኛ ትርፍ ሲያገኙ ቆይተዋል።
ይሁንና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ማብቃቱን ተከትሎ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ትርፍ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ ሰራተኛ ለመቀነስ ተገደው ቆይተዋል።
ፌስቡክ ብቻ 21 ሺህ ሰራተኞችን ቀንሷል የተባለ ሲሆን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ግን 34 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ተገልጿል።
የፌስቡክ፣ ዋትአፕ፣ ኢንስታግራም እና ትሪድስ ኩባንያዎች እናት የሆነው ሜታ ኩባንያ በዚህ ዓመት ያገኘው ገቢ ካምናው ጋር ሲነጻጸር የ23 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል።
ከሶስት ቢሊዮን በላይ ወርሀዊ አክቲቭ ደንበኞች ያሉት ሜታ ኩባንያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ መጠቀሙ እና የሰራተኛ ቅነሳ ማድረጉ ለገቢው ማደግ ዋነኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑም ተገልጿል።
ኩባንያው ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ 12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንዳገኘ አስታውቋል።
የኩባንያው ባለቤት እና መስራች የሆኑት ማርክ ዙከርበርግ ሰራተኞቻቸውን ያመሰገኑ ሲሆን በቀጣይ አዳዲስ አሰራሮችን በሁሉም ድርጅቶቻቸው በኩል እንደሚተገብሩ ገልጸዋል።
የ39 ዓመቱ ማርክ ዙከርበርግ በ111 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ ሀብት ሰባተኛው የዓለማችን ባለጸጋ አሜሪካዊ ቢሊየነር ናቸው።