የፌስቡክ ኩባንያ 100 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል ተከሰሰ
ድርጅቱ ክስ የቀረበበት በማህበራዊ ትስስር መተግበሪያው ህጻናትን የሚመለከቱ መልዕክቶችን አሰራጭቷል በሚል ነው
በኦሂዮ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ክስ የቀረበበት ፌስቡክ በህጻናት ላይ ባደረሰው ጉዳት 100 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል ክስ ቀርቦበታል
የፌስቡክ ኩባንያ 100 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍለ ተከሰሰ፡፡
የኩባንያውን ስም ወደ ሜታ የቀየረው ፌስቡክ 100 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል በኦሃዮ ፍርድ ቤት መከሰሱን የሩሲያው አርቲ ዘግቧል፡፡
ኩባንያው ክስ የቀረበበት በፈረንጆቹ 2021 ዓመት ውስጥ ካለፈው ሚያዝያ እስከ ጥቅምት ባሉት ወራት ውስጥ በፌስቡክ ህጻናትን ላልተገባ ጉዳት የሚያጋልጡ ጎጂ ይዘቶች በፌስቡክ በመተላለፋቸው መሆኑን የኦሂዮ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ዴቭ ዮስት ተናግረዋል፡፡
እንደ ክሱ ከሆነ ፌስቡክ በህጻናት ላይ አሉታዊ መልዕክቶች እንዳይዘዋወሩ መከላከል የሚያስችል አሰራር ቢተገብርም ትርፉን ለመሰብሰብ ሲል ተግባራዊ አለማድረጉ ተገልጿል፡፡
እነደ ዘገባው ከሆነ ፌስቡክ ላደረሰው ጉዳት 100 ቢሊዮን ዶላር እንዲከፍል እና የእርምት እርምጃዎችን እንዲወስድ ተጠይቋል፡፡
የሜታ ኩባንያ ቃል አቀባይ ጆ ኦስቦርን በበኩላቸው ክሱ በእውነት ላይ ያልተመሰረተ በመሆኑ ራሳችንን እንከላከላለን ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ፌስቡክ ላይ ክሱ የቀረበው የቀድሞ የኩባንያው ሰራተኛ አማካኝነት በወጣ ሪፖርት መነሻነት ሲሆን ፌስቡክ የተለያዩ ግጭት ቀስቃሽ እና ሌሎች የተለያዩ ማህበረሰብ አካላትን ሆን ተብለው የሚጎዱ መልዕክቶች ሲዘዋወሩ ኩባንያው ለትርፍ ሲል እርምጃ አልወሰደም የሚል ክሶች ቀርበውበታል፡፡
የሜታ ኩባንያ መስራች እና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ በበኩላቸው በድርጅታቸው ላይ የቀረበውን ክስ ውድቅ አድረገው ትርፍን እንደማያስቀድም ተናግረዋል፡፡