የፌስቡክ እለታዊ ተጠቃሚ ቁጥር 2 ቢሊየን ደረሰ
የሜታ እህት ኩባንያዎች የሆኑት ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ እለታዊ ጎብኝም ከምንጊዜውም በላይ መጨመሩ ተገልጿል
ሜታ በ2022 ከ11 ሺህ በላይ ሰራተኞችን መቀነሱ ይታወሳል
የሜታ እህት ኩባንያዎች ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ዋትስአፕ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከምንጊዜው በላይ ማደጉን የፌስቡክ መስራችና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ ተናግሯል።
ዙከርበርግ በፌስቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ፥ እነዚህ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በወር ከ3 ነጥብ 7 ቢሊየን በላይ ተጠቃሚ አላቸው።
የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በቀን 2 ቢሊየን መድረሱም ትልቅ እምርታ መሆኑን ነው ዙከርበርግ የጠቆመው።
ከ11 ሺህ በላይ ሰራተኞቹን ያባረረው ፌስቡክ በ2022 በርካታ ፈተናዎች ማሳለፉን በመጥቀስም ፥ ወርሃዊ የትስስር ገጹ ቋሚ ጎብኝዎችም 3 ቢሊየን መድረሱን በስኬትነት አንስቷል።
ኩባንያው በአመት ውስጥ ያገኘውን ትርፍ ከመጥቀስ የተቆጠበው ዙከርበርግ፥ የ2023 የፌስቡክ እቅድን ዘርዝሮ አቅርቧል።
በፌስቡክና ኢንስታግራም የሚለቀቀ አጫጭር ቪዲዮዎች (ሪልስ) በ2022 በእጥፍ ጨምረው የኩባንያውን ገቢም አሳድገዋል፤ በመሆኑም የ2023 ዋነኛ ትኩረታችን ከሪልስ የሚገኘውን ገቢ ይበልጥ ማሳደግ ነው ብሏል ዙከርበርግ።
በቀጣይ ጥቂት አመታት በፌስቡክ እና ኢንስታግራም ከግለሰቦች ወይም ተቋማት ከሚላኩ መልዕክቶች ጋር ማስታወቂያዎችን በመለጠፍ 10 ቢሊየን ዶላር ለማግኘትም ታቅዷል።
በ”ዋትስአፕ ቢዝነስ” ደግም ተቋማት ለደንበኞቻቸው መልክዕት የሚያደርሱበት፣ ጥያቄዎችን የሚመልሱበትና አገልግሎታቸውን በክፍያ የሚያሰራጩበት አሰራር ሌላው ትኩረት የሚደረግበት ነው ተብሏል።
ኤርፍራንስ በ22 ሀገራት በአራት ቋንቋዎች የጀመረው የመንገደኞች ትኬትን በዋትስአፕ የማድረስ አገልግሎትም ለአብነት ተነስቷል በማርክ ዙከርበርግ።
ሜታ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በቨርቹዋል ሪያሊቲ ዘርፍም በስፋት ለመስራት ማቀዱ ተገልጿል።