ሜታ የትራምፕን የፌስቡክ እና ኢንስታግራም አካውንት ከሁለት አመት በኋላ ሊከፍት ነው
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ማህበራዊ ትስስር ገጾች ከ2020ው የካፒቶል አዳራሽ ነውጥ በኋላ መዘጋታቸው ይታወሳል
ትራምፕ አሁንም ግጭት ቀስቃሽ መልዕክቶችን የሚለጥፉ ከሆነ ዳግም ይታገዳሉ ተብሏል
ሜታ የትራምፕን የፌስቡክ እና ኢንስታግራም አካውንቶች በቀጣዮቹ ሳምንታት እንደሚከፍት አስታውቋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት አካውንቶች ከሁለት አመት በፊት በካፒቶል አዳራሽ ከተፈጠረው ነውጥ ጋር በተያያዘ ታግደው መቆየታቸው ይታወሳል።
የትራምፕ የፌስቡክ እና ኢንስታግራም አካውንቶች ዳግም መመለስ በ2024 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለሚያደርጉት ፉክክር ትልቅ አበርክቶ ይኖረዋል ተብሏል።
ትራምፕ በፌስቡክ 34 ሚሊየን፤ በኢንስታግራም ደግሞ 23 ሚሊየን ተከታዮች አሏቸው።
ከ87 ሚሊየን በላይ ተከታዮችን ያፈራው የትዊተር ገጻቸውም ኤለን መስክ ኩባንያውን እንደገዙ ዳግም መከፈቱ አይዘነጋም።
የንግግር ነጻናት ተሟጋቾች የሜታን ውሳኔ የህብርተሰቡን መረጃ በነጻነት የማግኘት መብት ያከበረ ነው በሚል ደግፈውታል።
ሜታ ነውጥ ቀስቃሽ መልዕክቶችን በፍጥነት ከገጹ ላይ አያነሳም በሚል የሚወቅሱት ደግሞ ውሳኔው በደንብ ሊጤን እንደሚገባው እያሳሰቡ ነው።
የሜታ የአለም አቀፍ ጉዳዮች ፕሬዝዳንቱ ኒክ ክሌክ ግን፥ ትራምፕ በፌስቡክ እና ኢንስታግራም ገጾቻቸው ግጭት የሚቀሰቅሱ መልዕክቶችን ካጋሩ ከአንድ ወር እስከ ሁለት አመት ድረስ ሊታገዱ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ትራምፕ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት የ2020ው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መጭበርበሩን የሚገልጽ መልዕክት መነሳቱ ይታወሳል።
ያልተረጋገጠው መረጃቸው ደጋፊዎቻቸው ወደ ካፒቶል አዳራሽ በማምራት ነውጥ እንዲፈጥሩ ማድረጉም ነው በወቅቱ የተገለጸው።
በቀጣይ ሳምንታት ዳግም የፌስቡክ እና ኢንስታግራም አካውንቶቻቸው ሲከፈቱም የበሬ ወለደ መልዕክቶችን በማጋራት የአሜሪካን የዴሞክራሲ ስርአት አደጋ ላይ እንዳይጥሉት የሚሉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።
በአንጻሩ የማህብራዊ ትስስር ገጾቹ መከፈት ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳና የሃብት ማሰባሰብ ስራም ሆነ መረጃዎች በነጻነት እንዲንሸራሸሩ እድል ይፈጥራል የሚሉ ወገኖች አሉ።
ትራምፕ የትዊተር ገጻቸውን በህዳር ወር 2022 ቢከፈትም እስካሁን መረጃ አላጋሩበትም፤ ከዚህ በኋላ ምርጫቸው የራሳቸው “ትሩዝ ሶሻል” መተግበሪያ መሆኑንም ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጧል።
ወደ ፌስቡክ ዳግም መመለሳቸው ግን ለምርጫ ቅስቀሳቸው ከፍተኛ ሚና ስለሚኖረው ቸል ብለው ይተውታል ተብሎ አይጠበቅም።
በትሩዝ ሶሻል የትስስር ገጻቸው ላይም የፌስቡክ ገጻቸው ዳግም ሊመለስ መሆኑን ተከትሎ ባሰፈሩት ጽሁፍ “በየትኛውም በስልጣን ላይ ባለ ፕሬዝዳንት መሰል እርምጃ መወሰድ የለበትም” ብለዋል።
ሜታ ከትራምፕ ባሻገር የሌሎች ግለሰቦችን የተዘጉ የፌስቡክና የኢንስታግራም አካውንቶች ለመክፈት መዘጋጀቱንም ይፋ አድርጓል።