ፌስቡክ ኩባንያ በኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት የሁለት ቢሊዮን ዶላር ክስ ተመሠረበት
ክሱን ከመሰረቱት መካከል ፌስቡክ ላይ በተሰራጨ ቅስቀሳ ምክንያት አባቱ የተገደለበት ኢትዮጵያዊ ይገኝበታል
ፌስቡክ ክሱ የተመሰረተበት በኢትዮጵያ ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶችን አልተቆጣጠረም በሚል ነው
ፌስቡክ ኩባንያ በኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት የሁለት ቢሊዮን ዶላር ክስ ተመሠሰተበት።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ በሜታ ኩባንያ ስር ያለው ፌስቡክ ግጭት አባባሽ ይዘቶች እንደተሰራጩ ተገልጿል።
ፌስቡክ ኩባንያም ግጭት አባባሽ ይዘቶች ሲሰራጩ አልተቆጣጠረም፣ የማስተካከያ እርምጃም አልወሰደም በሚል ክስ እንደተመሰረተበት ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ ፌስቡክ ሀላፊነቱን ባለመወጣቱ ምክንያት በሰዎች እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷልም ተብሏል።
አብርሀም ማዕረግ የተባለ ግለሰብ በፌስቡክ የትስስር ገጽ ላይ በተሰራጨ ግጭት ቀስቃሽ ይዘት ምክንያት አባቱ እንደተገደለበት ለሚዲያው ተናግሯል።
ማእረግ አብርሀምን ጨምሮ ሌሎች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች የፌስቡክ ኩባንያ ባለቤት በሆነው ሜታ ላይ የሁለት ቢሊዮን ዶላር ክስ መመስረታቸውን ለዚሁ ሚዲያ አስታውቀዋል።
ሜታ ኩባንያ በበኩሉ የጥላቻ ንግግሮችን እና ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶችን ለማስወገድ ብዙ ገንዘብ ለቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መክፈሉን አስታውቋል።
ፌስቡክ የምስራቅ አፍሪካ ማስተባበሪያ ቢሮውን በኬንያ ናይሮቢ የከፈተ ሲሆን ጉዳት ደረሰብን ያሉት ኢትዮጵያውያኑም ክሳቸውን ናይሮቢ እንደከፈቱ ተገልጿል።
በሜታ ኩባንያ ላይ ክስ የመሰረቱት ኢትዮጵያዊያን በወቅቱ ፌስቡክ እየተሰራጩ ያሉ መረጃዎችን እንዲያጠፋ ቢያመለክቱም እርምጃ ሳይወስድ እንደቀረ ተናግረዋል።
ፌስቡክ በተለይም በአፍሪካ ጥላቻ ንግግሮችን እና ሀሰተኛ መረጃዎችን መከላከል የሚያስችል የሰው ሀይል እና ቴክኖሎጂ እንዳልመደበ ተገልጿል።
ይሁንና ፌስቡክ ኩባንያ በበኩሉ ብዙ ተናጋሪዎች ባሏቸው ቋንቋዎች በተለይም አማርኛ፣ ኦሮሚኛ እና ሌሎች ቋንቋዎች ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎች እንዳይሰራጩ ቋንቋውን የሚናገሩ ባለሙያዎችን ቀጥሮ በማሰራት ላይ መሆኑን ጠቅሷል።