ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የ533 ሚሊዬን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መረጃ በበይነ መረብ መለቀቁ ተነገረ
ይህ መሆኑ መረጃ ተጠቃሚዎችን ለተለያዩ የሳይበር ጥቃቶች እንዳያጋልጥ ተሰግቷል
ዝርዝር መረጃው በርባሪዎች (ሃከርስ) ተመንትፎ በነጻ በበይነ መረቦች ተለቋል ነው የተባለው
የበርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ዝረዝር መረጃዎች በበይነ መረብ መለቀቃቸው ተነገረ፡፡
መረጃዎቹ የተጠቃሚዎቹን ስምና የስልክ እንዲሁም የኢ-ሜይል አድራሻዎችን ጨምሮ ሌሎች ግለሰባዊ ሚስጥሮችንም ያካተቱ ናቸው ተብሏል፡፡
በመላው ዓለም ከሚገኙ የማህበራዊ ገጹ ተጠቃሚዎች የ533 ሚሊዬኑ ዝርዝር መረጃ ባሳለፍነው ቅዳሜ በበይነ መረብ በነጻ መለቀቁም ነው የተነገረው፡፡
ተጠቃሚዎቹ በ106 የዓለማችን ሃገራት የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡
32 ሚሊዬኑ ከአሜሪካ፣ 11 ሚሊዬኑ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ 6 ሚሊዬን ያህሉ ደግሞ በህንድ የሚገኙ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን ነው ዶቼ ቬለን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የዘገቡት፡፡
አለን ጋል የተባሉ እስራኤላዊ የመረጃ እና የሳይበር ባለሙያ ደግሞ የ14 ነጥብ 3 ሚሊዬን አፍሪካውያን የገጹ ተጠቃሚዎች መረጃ አለኝ የሚል መረጃን አጋርተዋል፡፡
የሃገራትን ዝርዝር የሚያስቀምጠው መረጃው የ11.5 ሚሊዬን አልጄሪያውያን ዝርዝር መረጃ እንዳለም ነው የሚጠቅሰው ምንም እንኳን ቁጥሩ እንደ አህጉር ካጋራው ጋር ቢለያይም፡፡
በሳዑዲ አረቢያ 28.8 ሚሊዬን፣ በቱርክ 19.6 ሚሊዬን ተጠቃሚዎች መረጃ ተለቋልም ይላል፡፡
በዝርዝሩ የኢትዮጵያ ስምም ተጠቅሷል፡፡
የ12 ሺ 753 ተጠቃሚዎች መረጃ መለቀቁንም ነው ልጥፉ (ፖስት) የሚጠቁመው፡፡
ይህ በመረጃ በርባሪዎች (ሃከርስ) ተመንትፎ የተለቀቀው መረጃ የማህበራዊ ገጹን ተጠቃሚዎች ለተለያዩ የሳይበር ጥቃቶች ሊያጋልጥ እንደሚችልም የመረጃ ደህንነት ባለሙያዎች አሳስበዋል፡፡
ፌስቡክ መረጃው “ተመንትፎ ነው” የመባሉን ጉዳይ አስተባብሏል፡፡ የመረጃው አስፈላጊነት ያን ያህል እንደሆነም ነው ቃል አቀባዩ ሊዛ ሼፈርድ በትዊተር የማህበረሰብ ገጻቸው ያስታወቁት፡፡
ቃል አቀባይዋ “ይህ ቀደም ሲል በ2019 ሪፖርት የተደረገ መረጃ ነው፤ ችግሩን በዚያው ዓመት ነሃሴ ላይ አስተካክለነዋል” ሲሉ ጽፈዋል፡፡
ሆኖም ብዙዎች ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ብዙዎችን ለዓይነተ ብዙ የመረጃ ጥቃቶች ሰለባ እንዳያደርግም ተሰግቷል፡፡
ፌስቡክ ከአሁን ቀደም ተመሳሳይ ችግሮች አጋጥመውታል፡፡
እ.ኤ.አ በ2018 ካምብሪጅ አናሊቲካ የተባለው የእንግሊዝ የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ ተቋም በብዙ ሚሊዬን የሚቆጠሩ የማህበረሰብ ትስስር ገጹን ተጠቃሚዎች መረጃ ከተጠቃሚዎቹ እውቅና ውጭ መጠቀሙ ይታወሳል፡፡
በዚህም ፌስቡክ 5 ቢሊዬን ዶላር እንደተቀጣ አይዘነጋም፡፡