ፌስቡክ በኢትዮጵያ እና ኬንያ የፖለቲካ ይዘት ባላቸው ማስታወቂያዎች ላይ ቁጥጥር ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ
በአዲሱ የፌስቡክ አሰራር ተጠቃሚዎች ማስታወቂያዎች ላይ በፍላጎታቸው መሰረት ገደብ መጣል ይችላሉ
ፌስቡክ ከምርጫና ፖለቲካ ጋር የተያያዙ ማስታወቂያዎች ላይ ኢትዮጵያና ኬንያን ጨምሮ በ98 ሀገራት ቁጥጥር ያደርጋል ተብሏል
ግዙፉ የማህበራዊ ሚዲያ ተቋም የሆነው ፌስቡክ ኢትዮጵያ እና ኬንያን ጨምሮ በሌሎች 98 የዓለማችን ሀገራት ፖለቲካዊ ይዘት ባላቸው ማስታወቂያዎች ላይ ቁጥጥር ሊያደርግ መሆኑን አስታውቋል።
ቁጥጥሩ በተለይም ከምርጫ ጋር የተገናኙ፣ ማህበራዊ እና ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በፌስቡክ ከመሰራጨታቸው በፊት ተጠቃሚዎች ያለ ፍላጎታቸው እና ምርጫቸው ወደ ገጾቻቸው እንዳይደርሱ የሚያደርግ እንደሆነ አፍሪካን ቢዝነስ ኮሚኒቲ በድረገጹ አስነብቧል።
ፌስቡክ ወደዚህ አሰራር የገባው ከአንድ ዓመት በፊት በአሜሪካ እና ብራዚል ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ ሲሆን ይህን አሰራር እስከ ቀጣዩ አንድ ዓመት ድረስ ኢትዮጵያ እና ኬንያን ጨምሮ በ98 የዓለማችን አገራት ላይ እንደሚተገበር ዘገባው ተጠቁሟል።
በፌስቡክ የአፍሪካ ፖሊሲ ዳይሬክተር ኮጆ ቦኪ እንዳሉት ከሆነ የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ተጠቃሚ ደንበኞች በተደጋጋሚ ያለፍላጎታቸው የፖለቲካ፣የምረጡኝ እና ማህበራዊ መልዕክቶች እንደሚደርሳቸው ተናግረዋል።
በአዲሱ የፌስቡክ አሰራር መሰረት ግን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በገጻቸው ገብተው ማስታወቂያዎች ላይ በፍላጎታቸው መሰረት ገደብ መጣል አልያም ማገድ እንዲችሉ ይፈቅዳል ተብሏል።