አምባሳደር ሱሌማን አነጋጋሪ ስለነበረው የፌስቡክ ጹሁፋቸው ምን አሉ?
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ የዲፕሎማቱ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ ሀገርን ትዝብት ውስጥ መጣል እንደሌለበት ገልጸዋል
አምባሳደር ሱሌማን “ዛሬም ከግብፅና ሱዳን ጋር የሚያናቁረን የምኒልክ ጦስ” ነው ብለው ጽፈው ነበር
አምባሳደር ሱሌማን “ዛሬም ከግብፅና ሱዳን ጋር የሚያናቁረን የምኒልክ ጦስ” ነው ብለው ጽፈው ነበር
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ በፈረንጆቹ ሰኔ 16 ቀን 2020 በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው አንድ ጹሑፍ ጽፈው ነበር፡፡
ይህ ጹሑፍ “ዛሬም ከግብፅና ከሱዳን ጋር የሚያናቁረን የሚንሊክ ጦስ” መሆኑ መዘንጋት የለበትም የሚል ነው፡፡
“በአባይ ወንዝ ላይ ከጣና ጀምሮ ምንም ዓይነት ግንባታ ላይገነባ፣ ወይም እንዲገነባ ላይፈቅድ ለእንግሊዞች የፈረመ አፄ ምኒልክ መሆኑ ተረሳ? ከሱዳን ጋር መፍታት ያልተቻለው ውስብስቡ የድንበር ችግር የምኒልክ ውርስ መሆኑ ቀረ እንዴ? ኢትዮጵያ ዛሬ ወደብ አልባ ሆና የቀረችው ያኔ በተፈፀሙ ታሪካዊ ስሕተቶች ምክንያት ነው። እንዴት ተደርጎ አሜሪካንን የሚያክል ትልቅ ሀገር የገነባን ጥበበኛ መሪ አብረሃም ሊንከንን የዘላለም መከራ አውርሶን ከሄደ ጨፍጫፊ ጋር ማወዳደር ይቻላል?“ ሲሉ አስፍረው ነበር፡፡
ይህ ጉዳይ በሀገር ውስጥ ያሉና በውጭ ሀገራት በሚኖሩ ዜጎች ዘንድ ከፍተኛ መነጋገሪያ መሆኑ ይታወሳል፡፡
አንዳንዶች ዲፕሎማቱ ደጋፊ በመሆን የጻፉት የግል ሃሳባቸውን ነው፤ ስለዚህ የሚያምኑበትን ስልጻፉ ምንም አዲስ ነገር አላደረጉም በሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ አምባሳደሩ የግላቸውን አቋም ቢያንጸባርቁም እርሳቸው የኢትዮጵያ ወካይ በመሆናቸው ይህንን ማለት ባልተገባ ነበር በሚል ተችተዋቸዋል፡፡
አምባሳደር ሱሌማን በፈረንጆቹ ሰኔ 16 በፌስቡክ የጻፉትን በተመለከተ ከአል ዐይን ጋር ባደረጉት ቆይታ “የሀገራችን ፖለቲካ የምታውቀው ነው፣ ለአንዱ የሚጥም ለአንዱ አይጥምም ፤ለአንዱ የሚመች ለአንዱ አይመችም፤ታሪካችን ብዙ ነገር ያለበት ነው፡፡ በታሪካችን ላይ ለመግባባት ራሱ ብዙ የሚቀረን ሕዝቦች ነን ስለዚህ እኔ የማምንበትን እንደ መብት የማይቆጥሩ እኔ በማያምኑበት የማያምኑ እኔን ሊተቹኝ ይችላሉ፤ መብታቸው ነው እኔ የማምንበትን ማራመድ መብቴ ነው፤ ስለዚህ የሆነ ነገር በአንድ ሰሞን ተፈጥሯል“ ብለዋል፡፡
“አሁንም እሱኑ በመድገም ማጋጋል የሚያስፈልግ አይመስለኝም ከሚያለያዩን ነገሮች ይልቅ በሚያግባቡን ነገሮች ላይ አተኩረን የሚያለያዩንን ቀስ እያልን እየተግባባንበት ጥሩ ነው የሚሆነው“ ያሉት አምባሳደሩ “እኔ በዚህ ጹሁፍ ማንም የገመገመኝ የለም” ምንም ያጠፋሁት ነገር የለም፣ የጻፍኩት አሁንም አለ አምኘበት ነው የጻፍኩት የማጠፋበት ምክንያት የለም የሚከፉ አለ አዎ አውቃለሁ የሚደሰቱም ይኖራሉ ትክክል ነው ፡፡
አሁን ላይ እርሳቸው ሁሉንም ኢትጵያዊ እንደሚወክሉና እንደሚያገለግሉና የሚወክሉትም ተችዎቻቸውንም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ሕዝቦች ሁሉ አንድ አይነት መከራ ተሸክመው የቆዩ በመሆናቸው አሁን ላይ ጫፍ የወጡት ሃሳቦች የሕዝቡ ሳይሆኑ የኤሊቶች ጨዋታ ስለመሆኑም ነው የሚገልጹት፡፡
አሁን ላይ ካለን ታሪክ ጥሩዎቹን እየገነባን መጥፎዎቹን ደግሞ ለታሪክና ለልምድ መተው እንደሚያስፈልግ የሚገልጹት አምባሳደር ሱሌማን “እኔ የትኛውንም ህዝብ የሚያስከፋ ስራ አልሰራም የኢትዮጵያ ህዝቦች አገልጋይ ነኝ“ በማለት አብራርተዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዋናው መ/ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች እና ቆንስል ጀኔራሎች ዓመታዊ ስብሰባ ሲጠናቀቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸው የዲፕሎማቱ የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ ሀገርን ትዝብት ወስጥ የሚጥል መሆን እንደሌለበትና ይህንንም ተቋሙ በሚገባ እንደሚከታተል ገልጸዋል ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ዲፕሎማቶቹ በመደበኛ ሚዲያዎችም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያዎች ያላቸው ተሳትፎ ማደግ እንዳለበት በውይይቱ መነሳቱንና ነገር ግን ይህ የሀገርን ገጽታ ለመገንባት መሆን እንዳለበት መግባባት መደረሱን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህ ዙሪያ አንዳንድ አላግባብ የሆኑ አዝማሚያዎች መኖራቸው በውይይቱ መነሳቱንና ይህም መስተካከል እንዳለበት ቃል አቀባዩ አንስተዋል፡፡