ፌስቡክ ከአንድ ዓመት በፊት በሌላ ተመሳሳይ ጥፋት 265 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት ተጥሎበት ነበር
ፌስቡክ የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዩሮ ቅጣት ተጣለበት፡፡
የሜታ ኩባንያ ንብረት የሆነው ፌስቡክ መረጃን አሳልፎ በመስጠት ወንጀል ተከሶ ነው የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዩሮ ቅጣት የተጣለበት፡፡
የአየርላንድ መረጃ መከላከል ኮሚሽን ላለፉት ዓመታት በፌስቡክ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ላይ ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቋል፡፡
ምርመራው ፌስቡክ የአውሮፓዊያንን መረጃ ለአሜሪካ አሳልፎ ሰጥቷል በሚል ሲደረግ የቆየ ሲሆን ጉዳዩ አሁን ላይ እልባት ማግኘቱን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በመሆኑም ኩባንያው የአውሮፓ መረጃ መከላከል ቁጥጥር አዋጅን ተላልፎ በመገኘቱ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዩሮ እንዲከፍል መወሰኑ ተገልጿል፡፡
በፌስቡክ ላይ የተጣለው የቅጣት ገንዘብ መጠን በአውሮፓ ታሪክ ከፍተኛው ነው የተባለ ሲሆን አማዞን ከዚህ በፊት የደንበኞችን መረጃ አሳልፎ ሰጥቷል በሚል 746 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት ተጥሎበት ነበር፡፡
ፌስቡክ ጥፋተኛ መሆኑን ተከትሎ ከተጣለበት ክፍያ በተጨማሪ በቀጣዩ አንድ ወር ውስጥ በአውሮፓ አገልግሎት እንዳይሰጥ እገዳ ሊጣልበት እንደሚችልም ተገልጿል፡፡
እገዳው የሚተላለፈው የምርመራው ውጤት አሜሪካ ፌስቡክን በመጠቀም አውሮፓዊያንን እየሰለለች ነው ወደ ሚል መደምደሚያ ሊወስድ ይችላል በመባሉ ነው፡፡
አሜሪካ እና አውሮፓ የመረጃ ልውውጥ ስምምነት ያላቸው ቢሆንም መረጃው ለስለላ ተግባር እንዲውል ግን ስምምነት እንደሌለ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
ሜታ ኩባንያ ከአንድ ዓመት በፊት የ533 ሚሊዮን ደንበኞችን መረጃ አሳልፎ በመስጠቱ የ265 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት ተጥሎበት ነበር፡፡