ፌስቡክና ኢንስታግራም በወርሃዊ ክፍያ “ሰማያዊ ባጅ” መስጠት ሊጀምሩ ነው
ትዊተር በህዳር ወር 2022 በወርሃዊ ክፍያ “የሰማያዊ ባጅ” መስጠት ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል
አገልግሎቱን ለማግኘት በወር 12 የአሜሪካ ዶላር መክፈል እንደሚገባ ሜታ አስታውቋል
የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ወርሃዊ ክፍያን በመክፈል “ሰማያዊ ባጅ” የሚያገኙበት አስራር በይፋ ሊጀምር ነው።
የፌስቡክና ኢንስታግራም እናት ኩባንያ ሜታ እንዳስታወቀው፥ በወር 11 ነጥብ 99 ዶላር በመክፈል የትክክለኛ አካውንት መለያ ሰማያዊ ጭረት ወይም (ሰማያዊ ባጅ) ማግኘት ይቻላል።
ለአይፎን ተጠቃሚዎች ደግሞ 14 ነጥብ 99 ዶላር ወርሃዊ ክፍያ ይጠየቃሉ ነው የተባለው።
የሜታ ዋና ስራ አስፈጻሚው ማርክ ዙከርበርግ በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው፥ አገልግሎቱ በተመሳሳይ ስም የሚከፈቱ ሀሰተኛ አካውንቶችን ለመለየትና የበይነ መረብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ያግዛል።
በዚህ ሳምንት በአውስትራሊያ እና ኒውዝላንድ የሚጀመረው አገልግሎት በቀጣይ ሳምንታትም በመላው አለም እንዲዳረስ እንሰራለን ነው ያለው ዙከርበርግ።
ሜታ ከዚህ ቀደምም በርካታ ተከታዮች ላሏቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች፣ አርቲስቶችና የቢዝነስ ተቋማት የሰማያዊ ባጅ ሲሰጥ ቆይቷል።
በዚህ ሳምንት ግን ለማንኛውም ትክክለኛ ማንነቱን የሚገልጽ መረጃ ላለውና ወርሃዊ ክፍያውን መክፈል ለሚችል ሁሉ አገልግሎቱን ማቅረብ ሊጀምር መሆኑን ነው ያስታወቀው።
የመለያ ምልክቷ የአካውንቱን ትክክለኛነት ከማመላከት ባሻገር የባለቤቱን ፖስቶች ተደራሽነት ለማስፋትም ትልቅ ድርሻ አላት ብሏል የፌስቡክ መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ።
በወርሃዊ ክፍያ የሚሰጠው አገልግሎት ከግለሰቦች ውጭ ለቢዝነስ ተቋማት ስለመቅረቡ ግን አልተገለጸም።
አዲሱ የሜታ ውሳኔ ከዚህ ቀደም የሰማያዊ ባጅ ያላቸውን የግለሰብ አካውንቶች እና ገጾች አይመለከትም ተብሏል።
በክፍያ የመለያ ምልክቷን መስጠት ምን ያህል የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ትክክለኛነት ያረጋግጣል የሚለው ጉዳይ ግን አጠያያቂ ነው።
ትዊተር በአሜሪካዊው ባለጠጋ ኤለን መስክ በተገዛ ማግስት የሰማያዊ ባጅ በወርሃዊ ክፍያ እሰጣለሁ ማለቱን ተከትሎ የተፈጠረውን ችግርም ያስታውሳሉ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች።
በወቅቱ በታዋቂ ሰዎች እና የንግድ ምልክቶች ስም ለተከፈቱ ሀሰተኛ አካውንቶች የሰማያዊ ባጅ እንዲሰጣቸው ክፍያ የፈጸሙ ሰዎች መበራከት ትዊተር አገልግሎቱን እንዲያቋርጥ ማድረጉን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።
ሜታ ግን የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ተጠቃሚዎች ሰማያዊ የመለያ ምልክቷን ለማግኘት ከስማቸው ጋር ተመሳሳይ የሆነ የመኖሪያ መታወቂያ ካርድ እና ሙሉ የፊት ገጽታቸውን የሚያሳይ ምስል ማቅረብ ይኖርባቸዋል ብሏል።
ከ11 ሺህ በላይ ሰራተኞቹን ባለፈው የፈረንጆቹ አመት ያሰናበተው ኩባንያው፥ አዲሱ አገልግሎቱ ገቢውን እንደሚያሳድግለት ይጠበቃል።